Monday, September 23, 2024
spot_img

የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልል ሕዝበ ውሳኔ መራዘም ቅሬታ አስነሳ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 4፣ 2013 ― የደቡብ ምዕራብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ የመራዘሙን ውሳኔ እንደማይቀበሉ የካፋ እና የዳውሮ ዞኖች ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ዞኖች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትላናትናው እለት የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ እንዲራዘም መወሰኑን ተከትሎ ተቃውሟቸውን የገለጹትን መግለጫ አውጥተዋል፡፡

የካፋ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እንዳሻው ከበደ በሰጡት መግለጫ ‹‹ለሕዝበ ውሳኔው አስፈላጊውe ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ባለበት ወቅት እንዲራዘም መወሰኑ ከዞናችን አኳያ ምንም ዓይነት መሠረታዊ ምክንያት የሌለው ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።

ቦርዱ ውሳኔውን በድጋሚ በማጤን ሕዝበ ዉሳኔው ቀደም ሲል በተያዘለት ሰኔ 14፣ 2013 እንዲካሔድ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ የካፋ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይ ተሠማ በበኩላቸው ‹‹ይህን ሕዝበ ውሳኔ የሚያስተባብሩ አመራሮች እንዲሁም የዞኖቹና የልዩ ወረዳው ከፍተኛ አመራሮች በጉዳዩ ላይ ሳይወያዩበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ በራሱና አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ህዝበ ውሳኔውን ማራዘሙ ተገቢነት እንደሌለው የዞኑ መንግሥት ያምናል›› ሲሉ ገልጸዋል።

የዳውሮ ዞን ደግሞ በሰጠው መግለጫ የሕዝበ ውሳኔው መራዘም ‹‹የዞኑን ነባራዊ ሁኔታ ፈፅሞ ያላገናዘበ እንዲሁም ለሃገረ መንግስት ግንባታ የዜግነት ግዴታቸዉን ለመወጣት በሞራልም ሆነ በስነልቦና የተዘጋጁትን ህዝባችንን ቅሬታ ዉስጥ ያስገባቸዉ ሆኖ አግኝተነዋል›› ብሏል።

ዳውሮ ዞን ምርጫ ቦርድ ለጳጉሜ 1 ያዘዋወረውን የድምጽ መስጫ ቀን ቀድሞ በተያዘለት ቀን ሰኔ 14 እንዲያደርግ አሳስቧል።

የደቡብ ምዕራብ ክልልን ለመመመስረት የሕዝበ ውሳኔ የሚያደርጉት የምዕራብ ኦሞ፣ የሸካ፣ የከፋ፣ የዳውሮ፣ የቤንች ሸኮ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img