Friday, November 22, 2024
spot_img

ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላን የያዘው የኢትዮጵያ ልኡክ ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያየ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 4፣ 2013 ― ✅ የኢፌዴሪ የፋይናንስ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ የመሩትና የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ተመስገን ጥሩነህን ያካተተው የመንግስት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማዔል ኡመር ጌሌህ ጋር በወቅታዊ አካባቢያዊና በሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ውይይት አካሄዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት የሁለቱ አገራት ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ታሪካዊ፣ የማይለዋወጥና በማናቸውም የውጭ ኃይል ተፅዕኖ የማይናወጥ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተለይም በትግራይ ክልል የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ፣ ሰብዓዊ ድጋፎችንም አጠናክሮ የማስቀጠልና መደበኛ የትምህርትና የግብርና ሥራዎችም እንዲጀምሩ የተደረገበት አግባብ መኖሩንም ነው የተባለው፡፡

በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ያለው ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረ መሆኑን ያነሱት የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማዔል ኡመር ጌሌህ ግንኙነቱ ታሪካዊ፣ ጠንካራና በማናቸውም የውጭ ተፅዕኖ የማይናወጥ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ጅቡቲ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን ለመፍታት እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀው የሁለቱ አገራት ትስስር ጠንካራ እንደሆነና መለያየት በማይችል መልኩ የተሳሰረ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአንዱ አገር ውስጥ የሚፈጠር ችግር ሌላውም ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ፕሬዝዳንቱ በውይይቱ ወቅት አንስተዋል፡፡

በመሆኑም ትሥሥሩን ይበልጥ ለማጠናከር ጅቡቲ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኗን ለልዑካን ቡድኑ አረጋግጠዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ኢታማጆር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከጅቡቲው አቻቸው ጄኔራል ዘካሪያ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ የመከላከያ ኃይሎች መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብና የመንግስታቱ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን አንስተው ይህንኑ ግንኙነት በወታደራዊ መስክም ማስቀጠል እንደሚገባ ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በወታደራዊ መስክ የመረጃ ልውውጥ፣ የትምህርትና ስልጠና ትብብር እንዲሁም የልምድ ልውውጦችን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በሁለቱ አገራት የጋራ ድንበርና የኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደርን ሰላማዊ ቀጠና ከማድረግ አኳያም በትብብር እንደሚሠሩ የተወያዩ ሲሆን ፣በዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ የጋር ሁለትዮሽ ውይይትም አጠናክረው ለማስቀጠል ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img