Sunday, September 22, 2024
spot_img

ባልደራስ የአቶ እስክንድር ነጋ ደኅንነት ስጋት ውስጥ ጥሎኛል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 2፣ 2013 ― ሊቀመንበሩ አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት የሚገኙበት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) የእስር ሁኔታቸው ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብኛል ብሏል፡፡

ፓርቲው በተለይ ከግንቦት 27፣ 2013 ጀምሮ አቶ እስክንድር ቀድሞ ታስረውበት ከነበረው ‹‹ዋይታ›› ተብሎ ከሚጠራው ዞን ደርሶባቸዋል ባለው የሰብዓዊ በደል ምክንያት 8ኛ ዞን ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ እንዲዛወሩ መደረጋቸውን አስታውሷል፡፡

ሆኖም አሁን ታስረው ባሉበት ቦታ በእስረኞች የደህንነታቸው ሁኔታ አደጋ ላይ እንደወደቀ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ማረሚያ ቤቱ ድረስ በመሄድ ለማረጋገጥ ችለዋል ነው ያለው፡፡

ፓርቲው አቶ እስክንድር ነጋ እየገጠማቸው ያለውን ‹‹የደህንነት አደጋ፣ ማረሚያ ቤቱም ሆነ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እያወቁ መፍትሄ ለመስጠት ባለመፈለጋቸው አዝኗል›› ያለ ሲሆን፣ ‹‹ችግሩ ከኦህዴድ/ብልጽግና የበላይ አካላት የተሰጠበት ፖለቲካዊ አቅጣጫ እንደሆነ የሚያሳይ ሆኖ አግኝተነዋል›› ሲል አስታውቋል፡፡

አክሎም ‹‹የቃሊቲ ማረሚያ ቤትም ሆነ በሕግ የእስረኞችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የአቶ እስክንድር ደህንነት አደጋ ላይ በመውደቁ ምክንያት ሊፈጠር ለሚችል ማናቸውም ነገር ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ማስገንዘብ እንወዳለን›› ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የእስክንድር ነጋ ደህንነት ኦህዴድ/ብልጽግና በፍትህ አደባባይ ለደረሰበት ውርደት መበቀያ ሳይሆን የመላ ሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ቀይ መስመር መሆኑን ተረድቶ፣ ለተፈጠሩ ችግሮች በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ›› በማለትም አሳስቧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img