Thursday, December 5, 2024
spot_img

ቦሪስ ጆንሰን የኮሮና ክትባት በመላው ዓለም እንዲዳረስ ኃያላን አገራት ላይ ጫና ሊያደርጉ ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 30፣ 2013 ― የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እስከ ቀጣዩ የአውሮፓዊያን ዓመት መጨረሻ ድረስ በመላው ዓለም የኮሮና ቫይረስ ክትባት እንዲዳረስ ጫና ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተሰምቷል፡፡

ይህንኑ እቅዳቸውን በመጪው ዐርብ በአገራቸው በሚደረገው የቡድን ሰባት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን እና ጃፓን ለዓለም አቀፉ የፍትሐዊ የክትባት ማከፋፈያ ፕሮግራም ኮቫክስ ምን ያህል ክትባት እንደሚያጋሩ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ እንግሊዝ እና ካናዳ ግን ምን ያህል አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ እስካሁን ይፋ አላደረጉም።

ከኮሮናቫይረስ ጋር እየተደረገ ያለውን ፍልሚያ በስኬት ለማጠናቀቅ እስከሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ በመላው ዓለም ክትባቱን ለማዳረስ ቦሪስ ለመሪዎቹ በኮርንዌሉ ጉባኤ ላይ ጥሪ ያቀርባሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ዓይነቱ ስኬት ‹‹በሕክምና ታሪክ ውስጥ ብቸኛና ታላቁ›› ይሆናል ብለዋል።

አገራቸው ዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱን የማምረት ምጣኔን እንዴት ከፍ ማድረግ እንደሚቻል የሚደረጉ ውይይቶችን እንደምታበረታታም ተገልጿል።

የቡድን ሰባት የመሪዎች ጉባኤ ከወረርሺኙ መከሰት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ገፅ ለገፅ የሚደረግ ሲሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሥልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ወደ እንግሊዝ የሚያደርጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ይሆናል፡፡

እንግሊዝ ምን ያህል ክትባት ለኮቫክስ እንደምታበረክት በጉባኤው ላይ ይፋ ታደርጋለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ባለፈው ሳምንት የፓርላማ አባላት ብሎም የአገራት መሪዎች እንግሊዝ የተያዘው የፈረንጆች አመት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቢያንስ 100 ሚሊዮን ክትባት እንድታበረክት ደብዳቤዎችን እንደፃፉላቸው ዘገባው አስታውሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img