Thursday, October 10, 2024
spot_img

የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎችን ላከ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 28፣ 2013 ― የአፍሪካ ኅብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት በደረሰው ጥያቄ መሠረት የአጭርና የረዥም ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድኖችን መላኩን የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት አስታውቀዋል፡፡

ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሰኔ 14 የሚካሄደውን አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ የሚታዘቡት ከተለያዩ የኅብረቱ አባል ሃገሮች የተውጣጡ ስምንት አባላት የሚገኙበት የረዥም ጊዜ ክትትል ቡድን ባለፉት ሁለት ቀናት አዲስ አበባ መግባቱን ኅብረቱ ባወጣው የፕሬስ መግለጫ አመልክቷል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው ቁልፍ የሚባሉ የምርጫ ሂደቱ ክፍሎች ላይ ቅኝት እንደሚያደርግና ትንተናም እንደሚሰጥ የጠቆመው መግለጫው፣ ይህም በተለይ የፖለቲካውን አየር፣ የምርጫውን የሕግ ማዕቀፍ፣ የምርጫ ዝግጅቱን ውጤታማነትና ግልፅነት እንዲሁም የአስተዳደርና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትንና በመላ ሂደቱ ውስጥም ለተሣትፎ መብቶች መከበር የሚሰጠውን ትኩረት ጨምሮ የዘመቻውን አካሄድ ሁኔታ እንደሚያካትት አስታውቋል።

ኅብረቱ የረዥም ጊዜ ታዛቢ ቡድኖች በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚሰማሩ የገለጸ ሲሆን፣ ምርጫው ሊካሄድ ወደ አንድ ሳምንት ሲቀር በርካታ የአጭር ጊዜ ታዛቢ ቡድኖች አዲስ አበባ እንደሚገቡም ገልጿል።

ለምርጫው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠማራው የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን፣ በኅብረቱ ድንጋጌዎች መሠረት በምርጫው ሂደት ላይ መረጃ የመሰብሰብና የመተንተን መብትና ችሎታ እንዳለው መግለጹን የዘገበው ቪኦኤ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img