Thursday, November 28, 2024
spot_img

አገር አቀፉን ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ግንቦት 26፣ 2013 ― ✅ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በቀጣይ ወር የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን ለአንድ ዓመት የዘለቀ ዝግጅት እንዳደረገ አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ምርጫው ከማንኛውም የደኅንነት ስጋት ነጻ እንዲሆን ሰባት ንዑስ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል ያሉ ሲሆን፣ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት፣ የምርጫ ጣቢያዎች፣ የምርጫ ወንጀል ክትትል ኮሚቴዎች እና ሌሎች አደረጃጀቶች ተደራጅተው ስራ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የፖስተር መቅደድ፤ እጩዎችን ማስፈራራት፤ የምርጫ ቁሳቁስ ስርጭቶችን ማወክ እና ሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች መፈጸማቸውንም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ምርጫው ተካሄዶ ውጤት ይፋ መሆን ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በተመለከተም ምክትል ኮሚሽነሩ ‹‹ምርጫ ቦርድ አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱን ይፋ ካደረገ በኋላ የጸጥታ ችግር ይከሰታል ብለን አንጠብቅም፤ የሚፈጠሩ ችግሮች ካሉ ግን የሰው ሃይል እና ለጸጥታ ማስከበር ስራ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን አድርገናል›› የሚል ምላሽ እንደሰጡት አል ዓይን አስነብቧል፡፡

በሌላ በኩል በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎችን በተመለከተም ‹‹ስጋቱ ባለባቸው ቦታዎች ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እርምጃ እየወሰደ እና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማድረግ ላይ ነው›› ሲሉ መልሰዋል። ፌደራል ፖሊስ ከምርጫ ውጤት ጋር በተያያዘ ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ህግ የማስከበር ስራውን ብቻ እንደሚያከናውንም ኮሚሽነር ዘላለም ተናግረዋል።

ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የፊታችን ሰኔ 14፣ 2013 እንደሚካሄድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img