አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 25፣ 2013 ― የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተሠማርተዋል መባሉን አስተባብሏል።
የክልሉ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ የኦሮሚኛ ቋንቋ እንደገለጹት በክልሉ እንደተባለው አንድም የኤርትራ ወታደር አልተሠማራም ብለዋል።
ሆኖም በክልሉ ሆሮ ጉድሩ ዞን አባይ ጮመን ወረዳ የሆኑ ነዋሪ ለዜና ተቋሙ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብስ ያደረጉ ትግርኛ ቋንቋ የሚናገሩ ወታደሮች አካባቢውን ማሸበራውን ተናግረዋል። እንደ ግለሰቡ ከሆነ ወታደሮቹ ሰዎችን የሚደበድቡ፣ የሚያስሩና ዝርፊያም የሚፈጽሙ ናቸው።
ነገር ግን በክልሉ በአሁኑ ወቅት የሚገኙት የአገር መከላከያ፣ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ እና የኦሮሚያ ሚሊሻ መሆናቸውን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ፣ ይህን የሚያስወሩት የአገር መከላከያ ኃይል በኦሮሚያ ክልል ድጋፍ ማድረጉ ደስ ያላሰኛቸው አካላት ናቸው ብለዋል።
አክለውም ለተነሳው የኤርትራ ወታደሮች በደል ይፈጽማሉ የሚል ቅሬታ የሸኔ አባላት የተለያዩ ወታደራዊ የደንብ ልብሶችን በመልበስ ድርጊቱን እንደሚፈጽሙና በሕወሃት ስለሚደገፉም ትግርኛም ሆነ ቋንቋ ሊናገሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በኦሮሚ ክልል የኤርትራ ወታደሮች ተሰማርተዋል የመባሉን መረጃ ይፋ ያደረገው ይኸው በመንግስት የተከከሰሰውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን የነበረ ሲሆን፣ ቡድኑ እንዳወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ጦር በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ጉጂ እና በቦረና ይገኛል ያለ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ይገኛል፡፡