አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 24፣ 2013 ― ግብጽ እና ሱዳን ለስድስት ቀናት ሲያደርጉ የነበረውን የምድር፣ የአየር እና የባህር ኃይሎችን ያሳተፈ የጦር ልምምድ በትናንትናው እለት ማጠናቀቃቸው ተነግሯል፡፡
ልምምዱ የሁለቱን ሀገራት የደኅንነት ግንኙነት ከማጠናከሩ ባለፈ ግብጽ እና ሱዳን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለገቡት ውዝግብ ኃይላቸውን ለማሳየት ተጠቅመውበታል ሲል አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል።
የስድስት ቀናቱ የጦር ልምምድ መቋጫ ሥነ ሥርዐት የሁለቱ ሃገራት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በተገኙበት ካርቱም ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ተካሂዷል የተባለ ሲሆን፣ ልምምዱ «የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ከማጠናከር በዘለለ በጋራ ሊቃጣባቸው የሚችል ስጋትን ለማስወገድ ያለመ ነው» ስትል ሱዳን በሰጠችው መግለጫ አስታውቃለች።
ሱዳን እና ግብጽ በተለይ የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ታይተዋል። የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለኢትዮጵያ ስጋት ሳያሳድር እንዳልቀረ ነው ዘገባው የጠቀሰው።