አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 24፣ 2013 ― የተባበሩት ዐረብ ኤሜሬት ከእስራኤል ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ከፍ ያደርጋል ያለቸውን የታክስ ስምምነት ፈጽማለች፡፡
እስራኤል በፍልስጤም ድንበር አካባቢዎች የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የተደረሰው የታክስ ቅናሾችንና ሌሎችን የያዘው ስምምነት በሚኒስትሮች እና በፓርላማ ከጸደቀ በኋላ ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ቀን አንስቶ ተፈጻሚ ይሆናል መባሉን ዴይሊ ሰባህ አስነብቧል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋቢ አሽኬናዚ የተደረሰው ስምምነት የሁለቱን አገራት ኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እስራኤል ባለፈው ዓመት ከተባበሩት ዐረብ ኤሜሬት እና ከባህሬን ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሟን ያስታወሰው ዘገባው፣ ስምምነቱን ተከትሎ የእስራኤል እና የኤሜሬት ባንኮች እንዲሁም ሌሎች ኩባንያዎች የትብብር ስምምነት ፈጽመዋል ብሏል፡፡
በእስራኤል እና በተባበሩት ዐረብ ኤሜሬት መካከል የተፈጸመው የሰላም ስምምነት በኋይት ሐውስ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሸማጋይነት መሆኑ አይዘነጋም፡፡