አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 23፣ 2013 ― በሁለት የጎንደር ከተማ የገጠር ቀበሌዎች ለቀናት የዘለቀው የተኩስ ልውውጥ ለማብረድ የአማራ ልዩ ኃይል እና መከላከያ ወደ አካባቢው ማቅናታቸው ተነግሯል፡፡
በጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ ጎንደርን ለማወክ በፈለጉ ኃይሎች ተፈጽሟል የተባለውና ካሳለፍነው ሳምንት የመጀመርያ ቀናት አንስቶ በጎንደር ከተማ ዙርያ የተሰማው ተኩስ “ቁስቋም” እና “ዳብርቃ” በተባሉ ቀበሌዎች ላይ የሆነ ነው፡፡
አዲስ ዘይቤ ድረ ገጽ እንዳስነበበው የተኩስ ልውውጡ ለቀናት ያህል ቀን እና ምሽት ሳይቋረጥ መሰማቱ ነዋሪዎችን አስግቷል፡፡ ሁነቱን ተከትሎ ከተገቢው የመንግሥት አካል ማብራሪያ በወቅቱ አለመሰጠቱ ነገሩን ከማባባሱም በተጨማሪ ያልተረጋገጠ መረጃ እንዲሰራጭ ምክንያት መሆኑንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
እንደ ጎንደር ከተማ ከንቲባ ከሆነ ተኩሱን የፈጸሙት ‹‹ጽንፈኛ የቅማንት ታጣቂ ሽፍቶች›› እና ‹‹የህወሓት ርዝራዥ›› ብለው የገለጹዋቸው አካላት ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት የመንግስት የጸጥታ አስከባሪዎች ሥፍራው እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
ይሁን እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት የከተማውም ሆነ የዙሪያው አስተዳዳር የፀጥታ ችግሮችን ቀድሞ መከላከል ላይ የክልሉና ያካባቢው መስተዳድሮች ድክመት እንዳለባቸው ይገልፃሉ። ከተማ መሀል ሰዎች እየተገደሉና እየታፈኑ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ መንግሥት ሕግ ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ተኩሱ ይሰማባቸዋል በተባሉት ‹‹ቁስቋም›› እና ‹‹ዳብርቃ›› በዜጎች ላይም ሆነ በንብረት ላይ ስለደረሰው ውድመት በይፋ የተነገረ ነገር የለም፡፡