አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 23፣ 2013 ― ባለፈው ሳምንት የምስክርነት ጥበቃቸው ተነስቶ ዳግም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው የተሰማው የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ መታዘዙ ተሰምቷል፡፡
ወይዘሮ ኬሪያ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ትእዛዝ የሰጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው፡፡
ይህንኑ ተከትሎም ከዚህ ቀደም በተጠረጠሩበት ወንጀል ከነ አቶ ስብሐት ነጋ ጋር ጉዳይ በጥምረት ጉዳያቸው እንዲታይ መታዘዙም ነው የተነገረው፡፡
በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሃት ሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ የፌዴራል ፖሊስ በተገኙበት ይያዙ የሚል ማዘዣ አውጥቶባቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ አሳይተውታል በተባለ የተባባሪነት ጠባይ ከተከሳሽነት ወደ ምስክርነት ተቀይረው ነበር።
ሆኖም ከቀናት በፊት ፍርድ ቤተ ቀርበው ለመንግስት ምስክር የመሆን ፍላጎት እንደሌላቸው እንዲሁም ምስክርነት ሲሰጡ የቆዩት ተገደው እንደነበር በመግለጻቸው ምስክርነታቸው መቋረጡን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡