Sunday, November 24, 2024
spot_img

ቀይ መስቀል ታግተው የነበሩ ቻይናውያንን ለኤምባሲያቸው መስጠቱን አረጋገጠ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 23፣ 2013 ― ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ከሳምንታት በፊት ታግተው የነበሩ ቻይናውያንን መቀበሉን አረጋግጧል፡፡

ቢቢሲ የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አልዮና ሳይኔንኮ ቀይ መስቀል ሦስቱን የቻይና ዜጎች ይዟቸው ከነበረው ታጣቂ ቡድን ተቀብለው ለአገራቸው ኤምባሲ አሳልፈው መስጠታቸውን ተናግረዋል ብሎ ዘግቧል፡፡

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ ከሚጠራውና መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለውና በቅርቡም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብር ቡድን ነው ብሎ የሰየመው ታጣቂ ቡድን፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ቻይናውያኑን በቁጥጥሩ ስር እንዳስገባ አሳውቆ ነበር።

ቡድኑ በምዕራብ ኦሮሚያ መነ ሲቡ ተብሎ በሚጠራው ወረዳ ውስጥ ያዝኳቸው ያላቸውን ሦስት የቻይና ዜግነት ያላቸውን ሰዎች መያዙን ከግለሰቦቹ ፎቶግራፍ ጋር አያይዞ ነበር፡፡

ሆኖም በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ አዲስ አበባ ያለው የቻይና ኤምባሲ ስለግለሰቦቹ በታጣቂው ቡድን እጅ መግባት በተመለከተ ያሉት ነገር አልነበረም።

ከሳምንታት በኋላ ቡድኑ ባሳለፍነው ቅዳሜ ቡድኑ ቻይናውያኑን መልቀቁንና ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ማስረከቡን የሚገልጽ በሰነድና በፎቶግራፍ የተደገፈ መግለጫ አውጥቷል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር (አይሲአርሲ) ሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰር አልዮና ሳይኔንኮ ማኅበሩ ሦስቱን ቻይናውያንን ተቀብሎ ለቻይና ኤምባሲ ማስረከቡን ጠቅሰው፤ ‹‹ማኅበሩ በኃላፊነቱ መሠረት ገለልተኛ ሆኖ ሦስቱ ቻይናውያን ከኦሮሞ ነጻነት ጦር ለቻይና ኤምባሲ ተላልፈው እንዲሰጡ አስተባብሯል›› ብለዋል።

የሕዝብ ግንኙነት ኦፊሰሯ አይሲአርሲ በጉዳዩ ላይ የነበረው ኃላፊነት ፍጹም ሰብዓዊነት ላይ የተመሠረት መሆኑን ገልጸው፤ ታግተው የነበሩት ቻይናውያን በሰላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

በግለሰቦቹ ጉዳይ የተጠየቁት የምዕራብ ወላጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ ኡመታ ከሁለት ሳምንት በፊት ‹‹በዞኑ ውስጥ ታግቶ የሚገኝ የውጭ ዜጋ የለም›› ብለው እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img