Wednesday, October 9, 2024
spot_img

በኢትዮጵያ የመጀመርያው ዓለም አቀፍ ሚዲያ ሊቋቋም ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 23፣ 2013 ― በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካ› የተሰኘ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ሊቋቋም እንደሆነ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ የተቋሙ መሥራች የሆነው ጋዜጠኛ ግሩም ጫላ ነግሮኛል ብሎ ዘግቧል፡፡

መቀመጫውን እና ዋናው መስሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ ከተማ ያደርጋል የተባለው ‹ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ ኦፍ አፍሪካ›፣ በ450 ሚሊዮን ብር ካፒታል በ5 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚያርፍ ተነግሮለታል፡፡

የሚዲያ ተቋሙ ሙሉ በሙሉ ስርጭቱን በእንግሊዝኛ ብቻ የሚጀምር ሲሆን፣ ለ24 ሰዓት ዜናዎች፣ ዶክመንተሪ፣ ቃለ መጠይቅ፣ የባህል እና መዝናኛ ዝግጅቶችን እንደሚያካትት ታውቋል።

ይህ ሚዲያ ለኢትዮጵያውን ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ለሚገኙ አፍሪካውያን ድምጽ እንደሚሆን የተናገረው ግሩም፣ አፍሪካውያን ብሎም ኢትዮጵያውያን ሀሳባቸውን የሚገልጹበት፣ የውስጥ ችግሮችን በአደባባይ የሚያሳዩበት እና የፈጠራ ሃሳቦችን ለምዕራባውያን የሚያስተላልፉበት ተቋም ይሆናልም ብሏል፡፡

የቴሌቪዥን ጣቢያው በ2 ዓመት ውስጥ ሁሉንም ደረጃዎች በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ይገባል የተባ ሲሆን፣ በነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ግንባታውን አጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት የተለያዩ አራት ደረጃዎች ይኖሩታል። የመጀመሪያው በማኅበራዊ ድረ ገጽ የተለያዩ ዝግጅቶችን ማሰራጨት ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ለስቱዲዮ ግንባታ የሚያስፈልጉ ዘመናዊ እቃዎችን የት እንደሚገኙ ዳሰሳ ማድረግ እና ለስቱዲዮ መገንቢያ የሚሆነውን መሬት መረከብ ነው።

ሦስተኛው ሁሉንም ግንባታዎች በታቀደው ልክ መገንባት ሲሆን፣ በመጨረሻም የስርጭት ተግባሩን ማስኬድ ነው ሲሉ መስራቹ አስረድተዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ ከሆነ GTNA በዚህ ዓመት የመጀመሪያውን ደረጃ ስርጭት በማኀበራዊ ድረገጾች ለማስጀመር አቅዷል።

ይህን ቦታ በሚረከቡበት ጊዜ ሚዲያውን ከማቋቋምም በላይ የልህቀት ማዕከል፣ ኦዲዮ ቪዥዋል ላይብረሪ እና ላብራቶሪ በተጨማሪም ለጋዜጠኞች መኖሪያ ቤት ለመገንባት ታቅዷል ሲል ጋዜጠኛ ግሩም ገልጿል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img