አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 20፣ 2013 ― የቀድሞው የጠኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እና የአሁኗ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የሐርቫርድ ቲ.ኤች ቻን የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የ2021 ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ አሸናፊ የሆኑት የሐርቫርድ ቲ.ኤች ቻን የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የ2021 ኔክስት ጄኔሬሽን ሽልማትን ነው፡፡
የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ በኢንተርኔት ታግዞ የተካሄደ ሲሆን፣ ሽልማቱን ያቀረቡት የፋኩልቲው ዲን ሚሼል ኤ. ዊሊያምስ፣ ዶ/ር ሊያ ለሽልማቱ የበቁት በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በወሰዷቸው ወሳኝ እርምጃዎች መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቱ የኔክስት ጄኔሬሽን ሽልማት አሸናፊ የሚሆኑትም በጠንካራ ራዕያቸው እና ተነሳሽነታቸው በዓለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽን ላይ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ወጣቶች መሆናቸውን ሚሼሌ ኤ. ዊሊያምስ ተናግረዋል።
በየትኛውም የዓለም ሀገራት ውስጥ የጤና ዘርፉን መምራት እጅግ ፈታኝ ነው ያሉት ሚሼሌ ኤ. ዊሊያምስ፣ ዶ/ር ሊያ ግን በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትርነትን ከያዙበት ቀን አንስቶ በተለይ በፈታኙ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሥራቸውን በብቃት የተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። ኮቪድ-19ን ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አንፃር በመንግሥት እና በግል ባለሃብቶች መካከል፣ በሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች እና በዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅቶች መካከል እንዲሁም በምሁራን እና በሌሎች ኢትዮጵያውያን መካከል የፈጠሩት አንድነት እና አብሮነት የሚያስደንቅ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የሐርቫርድ ቲ.ኤች ቻን የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ለዚህ የከበረ ሽልማት የመረጣቸው በመሆኑ የተሰማቸውን ክብር ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የሀርቫርድ ቲ.ኤች.ቻን ኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የ2021 ጁሊየስ ቤንጃሚን ሪችመንድ ሽልማትን ተቀብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዶክተር ሪችመንድን ምሳሌነት በመከተል የዓለምን ህዝብ ጤና በተለይም አቅመ ደካሞች ጤና ለማሻሻል በቻልኩት ሁሉ ለመስራት ቁርጠኛ ነኝ ብለዋል።