አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 20፣ 2013 ― በሶሪያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሽር አል አሳድ በመራጮች ከተሰጠው ድምጽ 95 ነጥብ 1 በመቶ ያህሉን አግኝተው በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት መመረጣቸው ተነግሯል፡፡
ይህንኑ ተከትሎም በሽር አል አሳድ ለቀጣዮቹ 7 ዓመታት ሶሪያን በፕሬዝዳንትነት ይመራሉ ተብሏል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ለ7 ዓመታት ሥልጣን ላይ የሚያቆየውን የሃገሪቱን ምርጫ ሲያሸንፉ የአሁኑ ለ4ኛ ጊዜ ነው፡፡
ከአሳድ ጋር ተቃዋሚ ሆነው በምርጫው የተወዳደሩ ሁለት ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ማለትም ዐብደላ ሳሙንና መሐመድ አሕመድ ደግሞ 1 ነጥብ 5 እና 3 ነጥብ 5 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡
ይህ ምርጫው በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ስር በሚገኙ ሰሜናዊ የሃገሪቱ አካባቢዎች ያልተካሄደ ሲሆን፣ እነዚሁ ተቃዋሚዎች ምርጫውን ቀልድ ነው ሲሉት ሰንብተዋል፡፡ በሌላ በኩል ከመራጮች ቁጥር ማነስ እና ከግልጸኝነቱ ጋር በተያያዘም የቅቡልነት ጥያቄዎች ሲነሱበት ነበር፡፡
ከሰባት ዓመታት ባስተናገደችው የእርስ በርስ ግጭት እንዳልነበረች የሆነችው ሶሪያ፣ የተፈናቀሉ በርካታ ዜጎች ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ሃገራት መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡