Sunday, September 22, 2024
spot_img

ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ሁሉን ያካተተ የፖለቲካ ምክክር እንዲደረግ ጠየቁ – ፕሬዝዳንቱ ጄፍሪ ፊልትማን በቀጣይ ሳምንት ወደ አፍሪካ ቀንድ አገራት በድጋሚ እንደሚመጡ ጠቁመዋል

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ግንቦት 19፣ 2013 ― የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅና ሀገሪቱን ወደመረጋጋት ለመመለስ ሁሉን አሳታፊ የፖለቲካ ምክክር አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት ይህ እንዲፈጸም ጠይቀዋል፡፡

በትግራይ ክልል የሚደረገው ጦርነት ያስከተለው ስብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን ያስታወሱት ባይደን፣ እየተፋለሙ ያሉ ወገኖች በአስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፣ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትና ተቋማት ለብሔራዊ እርቅና መግባባት ቅድሚያ ሰጥተው በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን በማቆም ወደ ውይይትና የጋራ ሀገራዊ መግባባት መድረስ አስፈላጊ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

በትግራይ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን በማንሳትም በኢትዮጵያ ከ1980ዎቹ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የረሀብ አደጋ በማንዣበቡ በጦርነቱ የሚሳተፉ ኃይሎች የሰላም መንገድ እንዲከተሉ፣ ዕርዳታ ያለምንም መስተጓጎል ለተቸገሩት እንዲደርስ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

አሜሪካ ከአፍሪካ ኅብረትና ከመንግሥታቱ ድርጅት ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላትም ባይደን አስታውቀዋል። ለዚሁ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፊልትማን በዚህ ሳምንት ወደ ቀጠናው እንደሚመጡ የፕሬዝዳንት ባይደን መግለጫ ጠቁሟል።

አሜሪካ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሁሉንም ሀገሮች ፍላጎት ያማከለ ስምምነት እንዲደረስ ፍላጎት እንዳላትም አመልክተዋል።

ፊልትማን ከቀናት በፊት የአካባቢውን ሀገራት ጎብኝተው ከቀጠናው መሪዎች ጋር ቢነጋገሩም ከኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች በኩል በጎ ምላሽ አላገኙም የተባለ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም አሜሪካ በሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት ላይ የጉዞና የኢኮኖሚ ማበረታቻ ማዕቀብ መጣሏ አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img