Saturday, September 21, 2024
spot_img

ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባን አስመልክቶ ለቀረቡ አቤቱታዎች ምላሽ ሰጠ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 17፣ 2013 ― ከፓለቲካ ፓርቲዎች በተመዘገቡ እጩዎች ላይ ያላቸውን ቅሬታ እና አቤቱታ ሲቀበል መቆየቱ ያስታወሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በዚሁ መሰረት ዋና ዋናዎች ያላቸውን ውሳኔ የተሰጠባቸው አቤቱታዎች በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል፡፡

ቦርዱ ይፋ ያደረጋቸው ሰባት ጉዳዮች ሲሆኑ፣ ከነዚህ መካከል የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ በወላይታ ዞን አቃቤ ህግ በእጩነት ተመዝግበዋል ብሎ አቤቱታ የቀረበው ጥያቄ ቦርዱ ተቀብሎ ለብልጽግና ፓርቲ የአቃቤህግነት ስራቸውን መልቀቃቸውን ወይም አቃቤ ህግ መሆን አለመሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቦርዱ መጠየቁን፣ የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብልፅግና ፓርቲ ካቀረባቸው እጩዎች መካከል የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ሀላፊ እንደሆኑና ይህም ከሕጉ ጋር እንደሚቃረን በመግለፅ ባቀረበው አቤቱታ መሰረት ቦርዱ ለብልጽግና ፓርቲ እጩው ስራውን መልቀቅ እንዳለባቸው ወይም እጩነታቸውን መተው እንደሚገባቸው ወስኖ ለፓርቲው ማቅረቡን አሳውቋል፡፡

በተመሳሳይ የጋምቤላ ህዝብ ነጻነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብልፅግና ፓርቲ በአኮቦ ወረዳ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ፣ በአቦቦ ወረዳ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሀላፊ፣ እንዲሁም በአቦቦ ወረዳ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት የክልሉ ሚሊሺያ ጽ/ቤት ሀላፊ መሆናቸውን እና ይህም ከሕጉ ውጪ መሆኑን በመግለፅ አቤቱታ አቅርቧል ያለው ቦርዱ፣ አቤቱታውን መርምሮ እና ህጉን ተመልክቶ ተቀባይነት እንደሌለው በመወሰን ለፓርቲው አሳውቄያለሁ ነው ያለው፡፡

ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሴያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በቀረበ አቤቱታ ብልፅግና ፓርቲ ካቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 31 በተደነገገው መሠረት ለእጩነት የሚያበቁ መመዘኛዎችን ተወዳዳሪው እንደማያሟሉ እና በምርጫ ክልሉ ለረጅም አመታት በስራም ሆነ በትምህርት ምክንያት እንዳልነበሩ በመግለፅ አቤቱታ ማቅረባቸውን ገልጾም፣ አቤቱታውን መርምሮ፤ ተወዳዳሪው በምርጫ ክልሉ መስፈርቱን ስለማሟላታቸው ተረጋግጦ በእጩነት ተመዝግበው ሠርተፍኬት የተሰጣቸው በመሆኑ እና ፓርቲው አቤቱታውን በወቅቱ ባለማቅረቡ አቤቱታው በቦርዱ በኩል ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን ለፓርቲው በደብዳቤ ማሳወቁን አስፍሯል።

ቦርዱ ይኸው ፓርቲ ኢሶዴፓ በሌላ አቤቱታ ለቦርዱ ባስገባው ደብዳቤ የብልፅግና ፓርቲ ካቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት በ2005 የአካባቢ ምርጫ የማረቆ ወረዳ ምክር ቤት በቆሼ አካባቢ ቀ/ገ/ማ የወረዳ ምክር ቤት ተመርጠው የነበሩ እና አሁን ደግሞ የወረዳ ምክር ቤት አባል እና የማረቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው በመስራት ላይ እንደሚገኙ በመግለፅ ከሕጉ ጋር ስለሚቃረን እንዲሰረዙ በማለት አቤቱታ አቅርቧል ያለ ሲሆን፣ አቤቱታውን በመመርመር እጩ ተወዳዳሪው የማረቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው መስራታቸው እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ከመቅረብ የሚያስቀራቸው ባለመሆኑ ፓርቲው ያቀረበው አቤቱታ በቦርዱ በኩል ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን ለፓርቲው አሳውቄያለሁ ብሏል፡፡

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) በበኩሉ ለቦርዱ ባስገባቸው ሁለት አቤቱታዎች በሰዳል ምርጫ ክልል የቀረቡ እጩ አድራሻቸው እንዲሁም የትውልድ ቦታቸው ከዚህ ምርጫ ክልል ውጪ መሆኑን በመግለፅ ከእጩነት እንዲሰርዙ፤ እንዲሁም ሌሎች እጩዎች ከማሽ ዞን ያሶ/ዛይ ወረዳ ለክልል ምክር ቤት ተወዳዳሪ የዞኑ ብልፅግና ሀላፊ በመሆናቸው፣ እንዲሁም የቡለን ምርጫ ክልል ተወዳዳሪ የክልሉ የፀረ-ሙስና ባለሙያ በመሆናቸው እንዲሰረዙ በማለት አቤቱታ ማቅረቡን አንስቶ፣ ቦርዱ አቤቱታውን መርምሮ የመጀመሪያው እጩ በምርጫ ክልሉ መስፈርቱን ስለማሟላታቸው ተረጋግጦ በእጩነት ተመዝግበው ሠርተፍኬት የተሰጣቸው በመሆኑ እና ፓርቲው አቤቱታውን በወቅቱ ባለማቅረቡ፣ እንዲሁም ሌሎቹ ሁለት እጩዎች የተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች በሕጉ መሠረት ከእጩነት የሚያስቀሩ ባለመሆናቸው አቤቱታዎቹ በቦርዱ ተቀባይነት ያለገኙ መሆኑን ለፓርቲው በተመሳሳይ በደብዳቤ ማሳወቀቁነ ገልጧል፡፡

ብልፅግና ፓርቲም ለቦርዱ ባቀረበው አቤቱታ የአፍዴር ዞን ምርጫ አስተባባሪ የሆኑት የቦርዱ ሰራተኛ አባታቸው እጩ መሆናቸውን በመጥቀስ ተቃውሞ በማቅረቡ፣ ቦርዱም ይህን አቤቱታ መርምሮ የምርጫ አስፈጻሚውን ጉዳይ፣ አስፈጻሚዎች ግምገማ በሚያደርግበት ወቅት በመገምገም እርምጃ እንደሚወስድ እጩው ግን በእጩነት እንዲቀጥሉ መወሰኑን ለፓርቲው ማሳወቁን ነው የገለጸው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img