Saturday, September 21, 2024
spot_img

እነ ሳፋሪኮም በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አስታወቁ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 17፣ 2013 ― አምስት ኩባንያዎች እና ተቋማትን ያካተተው ‹‹ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ›› የተሰኘው ጥምረት የሚያቋቁመው ኩባንያ፤ በኢትዮጵያ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የማቅረብ ሥራውን በሚቀጥለው ዓመት ጥር ወር 2014 ለመጀመር እንዳቀደ አስታወቋል።

በኬንያው ሳፋሪኮም የሚመራው ጥምረት ይህን ያስታወቀው በትላንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ነው። ጥምረቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድ ለመስጠት ያወጣውን ጨረታ ማሸነፉ በይፋ ከተገለጸ በኋላ መግለጫ ሲያወጣ የመጀመሪያው ነው።

የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፒተር ንዴግዋ፤ ‹‹የዲጂታል የአኗኗር ዘይቤ ለማቅረብ የቴሌኮም ኔትወርክ በመዘርጋት ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር የመስራት ዕድል በማግኘታችን ደስተኞች ነን። በኢትዮጵያ ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር በመስራት ተመሳሳይ ለውጥ ማቅረብ በዚያውም ለባለድርሻዎቻችን ዘላቂ ትርፍ ማስገኘት እንችላለን›› ሲሉ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ተስፋ እንደጣሉ የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል።

እንደ ሳፋሪኮም ሁሉ የጥምረቱ አባል የሆኑት የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮም እና የብሪታንያው ቮዳፎን፤ የቴሌኮም አግልግሎት በማቅረብ የሚታወቁ ግዙፍ ኩባንያዎች ናቸው። የቮዳኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ሻሜል ጆሱብ “የጥምረቱ አባላት፤ ጥራት ባለው የቴሌኮም ኔትወርክ የተገነባ ለውጥ የሚያመጣ የቴክኖሎጂ አገልግሎት በተለይም በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና ዘርፎች በማቅረብ የተመሰከረላቸው ናቸው” በማለት አምስቱ ኩባንያዎች እና ተቋማት የዲጂታል አገልግሎትን በማስፋፋት በኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ ‹‹ተጨባጭ ለውጥ›› የማምጣት ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የብሪታኒያው ቮዳፎን ዋና ስራ አስፈፃሚ ኒክ ሬድ በበኩላቸው ‹‹ይህ የቴሌኮም ውድድርን መፍቀድ ከመጨረሻዎቹ ግዙፍ የዓለም ገበያዎች አንዷ ለሆነችው ለኢትዮጵያ ትርጉም ያለው ለውጥ ነው። የሚቀጥለው ትውልድ የቴሌኮም እና የዲጂታል አገልግሎትን ስራ ላይ በማዋል የኢትዮጵያ ግዙፍ የኢኮኖሚ እና የልማት አቅም መሳካቱን ለማረጋገጥ እና አካታች እና ዘላቂ የዲጂታል ማኅበረሰብ ለመፍጠር ቁልፍ ሚና መጫወት እንፈልጋለን›› ብለዋል።

በ“ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ” ባለድርሻ የሆኑት የጃፓኑ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን እና የብሪታንያው የልማት ፋይናንስ ተቋም ኃላፊዎች ኢትዮ ቴሌኮምን ይገዳደራል ተብሎ የሚጠበቀው ኩባንያ ለኢትዮጵያውያን ደንበኞቹ ከኢኮኖሚያዊ ዕድገት የተቆራኘ ፋይዳ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል። የሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት እና ዋና የዲጂታል ኦፊሰር ቶሺካዙ ናምቡ ኩባንያው በእስያ እና በጃፓን ያካበተውን የዳበረ ልምድ እና እውቀት ወደ ኢትዮጵያ የመውሰድ ዕቅድ እንዳለው ጠቁመዋል።

የብሪታንያው የልማት ፋይናንስ ተቋም የአፍሪካ ቢሮ ኃላፊ ትንቢተ ኤርሚያስ በበኩላቸው ‹‹ከከተማ ነዋሪዎች እስከ ገበሬዎች፤ ለትላልቅ እና አነስተኛ ነጋዴዎች በአስር ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች የሚያቀርብ ዘመናዊ ኔትወርክ ለመዘርጋት ዝግጁ ነን›› ብለዋል። ‹‹ዘመናዊ፣ የተረጋጉ እና አዳጊ ኢኮኖሚዎች የተገነቡት በአስተማማኝ እና በተመጣጣኝ ዋጋ በሚቀርብ የዲጂታል መሰረተ ልማት፣ ለዓለም አቀፍ ንግድ ባለ ዕድል ላይ ነው፡፡ ሲሉም አገልግሎቱ የሚያመጣውን ትሩፋት ማስረዳታቸውን የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለሁለት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ ያወጣው ባለፈው ኅዳር 18፣ 2013 እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img