Monday, September 23, 2024
spot_img

መንግሥት ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት በድጋሚ ለማጤን እንደሚገደድ አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 16፣ 2013 ― የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ ማእቀብ መጣሉን ማስታወቁን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ የአሜሪካን ውሳኔ ተከትሎ መንግስት ከአገሪቱ ጋር ያለውን ግንኙነት በድጋሚ ለማጤን እንደሚገደድ ገልጧል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አክሎም በዚህ ምርጫ ባለበት ወቅት መንግሥት ድጋፍ እንጂ እንዲህ ዓይነቱን መጥፎ ጥላ የሚያጠላ ውሳኔ አይጠብቅም ነበር ያለ ሲሆን፣ የአሜሪካን በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት በማንሳት ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮቿን እንዴት እንደምታስተዳድር የሚነገራት አገር አለመሆኗም አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል መግለጫው የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን መንግስት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ሕወሃት ጋር ባንድነት መበየኑንም የሚያሳዝን መሆኑንም ገልጧል፡፡

ጨምሮም የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ በሚመጣ ግፊት ሳይሆን በራሱ ተነሳሽነት ብሔራዊ ንግግር እያደረገ ይገኛል ያለው የውጭ ጉዳይ፣ በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ግን መንግስት ሊደራደር አይችልም ብሏል፡፡

በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙትን ተጠያቂ ለማድረግ ባለው ዝግጁነት መሠረት ኢሰመኮ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ምርመራ ለመድረግ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውንና በትግራይ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ያልተገደበ የሰብአዊ አቅርቦት እንዲኖር ክፍት ማድረጉንም አንስቷል፡፡

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትላንት ምሽት በኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን በኩል ባወጣው መግለጫ አገሪቱ በኢትዮጵያና በኤርትራ የአሁን እና የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ በወታደራዊና የደኅንነት ሹማምንት፣ በአማራ ክልል አስተዳደርና የፀጥታ መዋቅር መሪዎች እንዲሁም የሕወሓት መሪዎች ላይ የጉዞ ማዕቀብ መጣሏ መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡

ይህ በባለሥልጣናት ላይ የተጣለው ማእቀብ ባለስልጣናቱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውንም የሚያካትት መሆኑን መግለጫው ያመለክታል፡፡

አሜሪካ ማዕቀቡን ለመጣል የወሰነችው በትግራዩ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መሬት ላይ ለቀው እንዲወጡ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እንዲሁም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ በተደጋጋሚ ዲፕሎማሲዊ ውትወታ ባደርግም ሐሳቡ ተቀባይነት አላገኘም በሚል ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img