አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 16፣ 2013 ― የኤርትራ መንግሥት ከካታር ብሔራዊ ባንክ በፈረንጆቹ 2009 የተበደረውን ገንዘብ ለመክፈል ፍቃደኛ እንዳልሆነች ተነግሯል፡፡
ሪክሌም ኤሪትሪያ የተባለ ድረ ገጽ ይዞት እንደወጣው ዘገባ ከሆነ የኤርትራ መንግሥት ከካታር ብሔራዊ ባንክ በፈረንጆቹ በ2009 30 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ሲበደር በ36 ወራት እመልሰዋለሁ ባለው ስምምነት ላይ በሁለቱ አካላት መካከል አለመግባባት ቢፈጠር በእንግሊዝ ሕግ ለመገዛት ተዋውሎ ነበር፡፡
የኤርትራ መንግሥት ከስምምነቱ በኋላ ወዲያው ቀድሞ የተበደረው 36 ሚሊዮን ዶላር ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር እንዲያድግ በመጠየቅ የብድር አከፋፈሉንም በሩብ ዓመት ከፋፍሎ ለመመለስ ተስማምቶ ነበር፡፡
ይህንኑ ስምምነት መሠረት በማድረግ የኤርትራ መንግሥት ለሁለት ጊዜያት ብድሩን የከፈለ ቢሆንም፣ በ2012 ግንቦት ወር ከመለሰው 19 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር በኋላ ሊከፍል እንዳልቻለ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የኤርትራ መንግሥት ክፍያውን ማቆሙን ተከትሎ ከአምስት ዓመታት በኋላ በ2017 የካታር ብሔራዊ ባንክ ገንዘቡ እንዲከፈለው ደብዳቤ የጻፈ ቢሆንም፣ ከአስመራ በኩል ምላሽ ተነፍጎታል፡፡ ሆኖም ለሁለተኛ ጊዜ በጻፈው ደብዳቤ የኤርትራ መንግሥት እዳውን አምኖ ባንኩ እንዲታገሰው ጠይቋል፡፡
ነገር ግን የካታር ብሔራዊ ባንክ የኤርትራ መንግሥት ቃል እንደገባው ሊፈጽም ባለመቻሉ ጉዳዩን በመጀመሪያ በእንግሊዝ ፍርድ ቤት፣ ኋላም ወደ አሜሪካ ፍርድ ቤት ወስዶት የኤርትራ መንግሥት የተበደረውን እዳ ክፍያ ከነ ወለዱ ጭምር ከ286 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲከፈለው የተወሰነለት ቢሆንም፣ የኤርትራ መንግስት ፍቃደኛ ባለመሆኑ የካታር ብሔራዊ ባንክ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝን የኤርትራ መንግሥት ንብረት በመውሰድ በምትኩ የማስመለስ ፍቃድ አግኝቷል፡፡
የኤርትራ መንግሥት ከካታር ብሔራዊ ባንክ የተበደረውን ገንዝብ ለምን መመለስ እንዳልፈቀደ በይፋ ያለው ነገር ስለመኖሩ በዘገባው አልተጠቀሰም፡፡