Monday, September 23, 2024
spot_img

አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ እቀባ ጣለች – አገሪቱ ሌሎች መንግሥታትም እርምጃውን እንዲቀላቀሉ ጠይቃለች

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 16፣ 2013 ― የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን በኩል ባወጣው መግለጫ አገሪቱ በኢትዮጵያና በኤርትራ የአሁን እና የቀድሞ ባለሥልጣናት፣ በወታደራዊና የደኅንነት ሹማምንት፣ በአማራ ክልል አስተዳደርና የፀጥታ መዋቅር መሪዎች እንዲሁም የሕወሓት መሪዎች ላይ የጉዞ ማዕቀብ ጥላለች፡፡

ይህ በባለሥልጣናት ላይ የተጣለው ማእቀብ ቤተሰቦቻቸውንም የሚያካትት መሆኑን መግለጫው ያመለክታል፡፡

የጉዞ ማዕቀቡ የትኞቹን ባለሥልጣናት እንደሚመለከት መግለጫው አልዘረዘረም። አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ባለስልጣናትና በሕወሓት አንዳንድ አባላት ላይ የተጣለው እገዳ የጠቀሰው ደንብ ቁጥር (Section 212a) ሲሆን፣ በዚህ ደንብ መሰረት የማዕቀቡ ዒላማ የሆኑት ባለሥልጣናትን ስም ለሕዝብ ይፋ ማድረግን አይጠይቅም።

በዚሁ መግለጫ ላይ እንደተመላከተው ከባለሥልጣናቱ የጉዞ ማእቀብ ተጨማሪ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ትሰጥ የነበረውን የኢኮኖሚ ማበረታቻና የፀጥታ ድጋፍ የምታቋርጥ ይሆናል፡፡ ሆኖም የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲሁም ለትምህርት፣ ግብርና እና ጤና ለመሳሰሉት የሚደረገው የልማት ዕርዳታ ግን ይቀጥላል።

አሜሪካ ማዕቀቡን ለመጣል የወሰነችው በትግራዩ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ መሬት ላይ ለቀው እንዲወጡ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እንዲሁም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ በተደጋጋሚ ዲፕሎማሲዊ ውትወታ ባደርግም ሐሳቡ ተቀባይነት አላገኘም በሚል ነው።

በመግለጫው ላይ አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላይ የተሳተፉ እና በክልሉ የሰብአዊ አቅርቦት እንዳይዳረስ የሚያደርጉትን ተጠያቂ እንዲያደርግ የጠየቀች ሲሆን፣ የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚገኙ ወታደሮቹን ወደ ኤርትራ ድንበር ይመልስ ብላለች፡፡

በሌላ በኩል አሜሪካ አሁንም ቢሆን በትግራይ ተፋላሚ ኃይሎች በትግራይ ጦርነቱን አቁመው የሰብአዊ አቅርቦት በፍጥነት እንዲደርስ ካልተደረገ አሁን የሚታየው የምግብ እጥረት በርትቶ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቃለች፡፡

አሜሪካ በዚሁ መግለጫ ላይ አሁን የወሰደችውን እርምጃ ሌሎች መንግሥታትም እንዲቀላቀሉ የጠየቀች ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለተፈጠሩ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲበጅለትም ስትል አሳስባለች፡፡

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት በትግራይ ጦርነት የሚሳተፉ ወገኖች ላይ የጉዞና የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንዲደረግ የሚጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የጣለውን እቀባ ተከትሎ በመንግሥት በኩል ይህ ዘገባ እስከተሰናዳበት ሰአት ድረስ የተባለ ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img