Sunday, October 6, 2024
spot_img

በኢትዮጵያ የሚሠራጩ የሃይማኖት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ተመዝግበው ፍቃድ ሊሰጣቸው ነው

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ግንቦት 15፣ 2013 ― የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሃይማኖት የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን መመዝገብ ሊጀምር ነው። ከአስር ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚጀመረው ምዝገባ ለአንድ ወር ያህል ይቆያል መባሉን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አቶ መሐመድ ኢድሪስ ምዝገባው ያስፈለገበት ምክንያት በመጋቢት 2013 በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ስራ ላይ የዋለው አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፤ የሃይማኖት ተቋማት የብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ እንዲያገኙ በመደንገጉ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት የጸደቀው አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ “የሃይማኖት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ እንደማይሰጣቸው” የሚደነግገውን የቀድሞውን የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ በመሻር ተቋማቱ በብሮድካስት አገልግሎት እንዲሳተፉ ፈቅዷል።

የሃይማኖት ቴሌቪዝን ጣቢያዎቹ ከአስር ቀናት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ይፋ በሚደረገው የምዝገባ ጥሪ መሰረት ለመመዝገብ ሲመጡ ሶስት ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አቶ መሐመድ ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ፤ የቴሌቪዥን ጣቢያው አስተምህሮቱን የሚያስተላልፍለት የሐይማኖት ተቋም በሰላም ሚኒስቴር የተመዘገበ መሆን ነው። ሁለተኛው የሐይማኖት ተቋሙ ለጣቢያው የሚሰጠው የድጋፍ ደብዳቤ ሲሆን፤ የመጨረሻው መስፈርት ደግሞ እንደማንኛውም የንግድ ድርጅት ከሚመለከተው የመንግስት አካል የሚሰጥ ዕውቅና ነው።

በአዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የተሰጣቸውን መብት ተጠቅመው የሚመዘገቡ የቴሌቪዝን ጣቢያዎች “ተገቢውን ጥበቃ እና እገዛ ያገኛሉ” ሲሉ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “በተሰጠው ቀነ ገደብ የማይመዘገቡ ጣቢያዎችን እንደ ህገ ወጥ ነው የምናያቸው” የሚሉት አቶ መሐመድ፤ “ህገ ወጥ ተቋማቱን ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንሰራለን” ሲሉ በቁጥጥሩ ላይ ዐቃቤ ህግ እና ፖሊስ ጭምር እንደሚሳተፉበት አስታውቀዋል።

ከሃይማኖት የመገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ ለበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ዕውቅና የሰጠው አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው በጥር 2013 መጨረሻ ነው። የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ፤ ቀደም ሲል የመገናኛ ብዙኃንን ምዝገባ እና ፍቃድ ሲያስፈጽም የነበረው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ስያሜውን ወደ ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን መቀየሩን ዘገባው አስታውሷል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img