Monday, October 7, 2024
spot_img

በደምቢዶሎ በተረሸነው ወጣት ቤት የተገኙ ለቅስተኞችን ፖሊስ ማሰሩ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 14፣ 2013 ― ከአስር ቀናት በፊት በምዕራብ ኦሮሚያ ደምቢዶሎ ከተማ በመንግሥት የፀጥታ አካላት በአደባባይ የተረሸነው አማኑኤል ወንድሙ የተባለ ወጣት ወላጆች መኖሪያ ቤት የተገኙ ለቀስተኞች መታሠራቸውን አዲስ ስታንዳርድ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

ድረ ገጹ በዘገባው ከወጣቱ ዘመድ ሰምቻለሁ እንዳለው ወጣቱ ከተገደለ በኋላ የጸጥታ ኃይሎች በአማኑኤል ቤተሰቦች ላይ የተለያዩ እንግልቶች ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡

እነዚሁ የጸጥታ አካላት ለለቀስተኞች የተዘጋጀውን ድንኳን እንዲፈርሱ መጠየቃቸውን የሚናገሩት ወሬ ነጋሪው፣ ይኸው ትእዛዝ በትላንትናው እለት ከአራት የኦሮሚያ ፖሊስ አባት ጋር ወደ ለቅሶ ቤቱ በዘለቁት የከተማው ከንቲባ ጭምር መተላለፉን ገልጸዋል፡፡

ከንቲባው ትእዝዝ ሰጥተው ከሄዱ ጥቂት ቆይታ በኋላ የፀጥታ አካላቱ ኃይል ጨምረው በመኪና ተመልሰው በመምጣት የቤተሰብ አባላትንና ለቀስተኞችን ጭነው መውሰዳቸውም ነው የተነገረው፡፡

35 የሚጠጉ ለቀስተኞቹ በጸጥታ አካላት ከተወሰዱ ሰአታት ቆይተው የተለቀቁ ቢሆንም፣ የሟች አባት የሆኑት አቶ ወንድሙ ከበደ እና ሌሎች ሁለት ዘመዶቻቸው አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ በዘገባው ተመላክቷል፡፡

የፖሊስ አባላቱ ከወሰዷቸው ለቀስተኞች መካከል የሟቹ አማኑኤል ወንድሙን የስድስት ዓመት እድሜ ያላት ሕፃን ጨምሮ ሽማግሌዎችም ይገኙበታል ነው የተባለው፡፡

በሃያዎቹ መጀመርያ እድሜ ላይ ይገኝ የነበረው አማኑኤል ወንድሙ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሕዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ በጥይት ተደብድቦ የተገደለው የ‹አባ ቶርቤ› ቡድን አባል ነው በሚል መሆኑ መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡

በወቅቱ የወጣቱን ግድያ ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከሕግ ውጭ የተደረገ ነው ያለውን ይህንኑ ግድያ ማውገዙ አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img