አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 13፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ አብዛኛው የዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አሳውቀዋል፡፡
ሕዝበ ውሳኔው አጠቃላይ ምርጫው ከሚካሄድበት ቀን ጋር አንድ ላይ እንደሚካሄድ ገልፀዋል። ለአጠቃላይ ምርጫውና ለሕዝበ ውሳኔው አንድ የምርጫ መዝገብ የተዘጋጀ ሲሆን፣ መራጮች ለምርጫውም ለሕዝበ ውሳኔውም አንድ ላይ ድምጽ ይሰጣሉ ብለዋል።
በዞኖቹና በልዩ ወረዳው ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የተመዘገቡ ሰዎች ለሕዝበ ውሳኔው እንደተመዘገቡ የሚቆጠር በመሆኑ ለሕዝበ ውሳኔው የሚሳተፉ ሰዎች ምዝገባ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ባለው አሰራር መሰረት ለምርጫውና ለሕዝበ ውሳኔው የድምጽ መስጫ ወረቀት ተዘጋጅቶላቸው ድምጻቸውን ይሰጣሉ።
ለሕዝበ ውሳኔው የተዘጋጀው የድምጽ መስጫ ወረቀት በኅትመት ላይ እንደሚገኝና ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የታተመው የድምጽ መስጫ ወረቀት በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰራጨት ሲጀመር ወደ ዞኖቹና ወደ ልዩ ወረዳው በሚገኙ የምርጫ ክልሎች በልዩ ሁኔታ እንደሚላክ አስረድተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ቦርዱ እስካሁን ምንም አይነት አቤቱታ እንዳልደረሰው ወይዘሪት ሶልያና ተናግረዋል።
ለሕዝበ ውሳኔው የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ለአጠቃላይ ምርጫው የተመዘገቡ ሰዎች አሃዝ ተጠቃሎ ሲመጣ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚካሄድበት ቀን ወደ ሰኔ 14፣ 2013 እንዲራዘም በመደረጉ ሕዝበ ውሳኔው በምርጫው ቀን እንደሚከናወን ማግለፃቸውን የዘገበውን ኢዜአ ነው፡፡