አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ግንቦት 12፣ 2013 ― ኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል ካቀደችው 6 ቢሊዮን ችግኞች በተጨማሪ አንድ ቢሊዮን ችግኝ ለጎረቤት አገራት ልታድል መሆኑ ተነግሯል፡፡ በመርሃ ግብሩ መሠረት ከኢትዮጵያ ችግኝ የሚሰጣቸው ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኬንያ ናቸው፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሐሰን እንደገለጹት መርሃ ግብሩ ከጅቡቲ የሚጀመር ሲሆን፣ በቀጣይነት ወደ ሌሎች አገራት የሚተላለፍ ነው፡፡
ለጎረቤት አገራት ከሚሰጡት አንድ ቢሊየን ችግኞች መካከል ወደ 780 ሚሊዮን የሚሆኑት ችግኞች ዐይነታቸውም ሆነ የሚፈልጉት የአየር ንብረት የተለየ መሆኑን እና በቅርብም ማከፋፈል እንደሚጀመር ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የግብር ሚንስትሩ ዕቅዱ በኢትዮጵያ አነሳሽነት የሚተገበር መሆኑን በመጥቀስ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ናት ሃሳቡን ያነሳቸው እንጂ ሃገራቱ ይህ ይሰጠን ብለው አይደለም›› ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጎረቤት አገራትን ማካተቱ የዲፕሎማሲ አካል መሆኑን ያስተወሱት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የባህል ዲሎማሲም ዓይነት ነው። ከሌላ ሥጦታም በላይ ተመሳሳይ ሥራ አብሮ ቢሰራ ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል በሚል ነው›› ሲሉ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የግብርና ሚንስትሩ ዑመር ሐሰን በአገር አቅፍ ደረጃ የሚተከሉት 6 ቢሊዮን ችግኞች በክልል ከተሞች እና በከተማ ዳርቻ አካባቢ ባሉት ቦታዎች እንደሚሆን ተናግረው፤ የክልሎች የችግኞች ድርሻ የሚወሰነው በዝግጅታቸው ልክ ይሆናል ያሉ ሲሆን፣ ደን ለመፍጠር ከሚያስችሉ ችግኞች ጎን ለጎን በአጭር ጊዜ ጥቅም የሚሰጡ እንደ አቮካዶ እና ፓፓዬ ያሉትም እንደሚተከሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹ቁጥሩ ከፍ ሲል ሰዉ በደን መልክ ብቻ ስለሚያስብ በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ ለሌላ ጥቅም ሲያውለው የነበረውን እና ከ3-5 ዓመት እየተከለ የሚጠቀምበትን ማለት ነው። ፍሬውን ሸጦ የሚጠቀምበት ዓይነት ዝርያዎችንም እንዲኖሩ ተደርጎ ነው የተዘጋጀው›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ከትላንት በስትያ ይህን የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ባስጀምሩበት ወቅት የአካባቢ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ የወጣው የአራት ዓመት እቅድ አካል መሆኑን ገልጸው ነበር።