አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ግንቦት 12፣ 2013 ― አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የጋዛ ታጣቂዎችና የእስራኤል ባለሥልጣናት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊፈርሙ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
በቅርብ ሰዓታት ውስጥ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ሙሳ አቡ መርዙቅ ለሊባኖሱ ማያዲን ቲቪ በሰጡት ቃለምልልስ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ፈር እየያዘ በመጠቆም፣ ‹‹ከሁለት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ስምምነት የምናደርግ ይመስለኛል›› ብለዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ በጋራ መግባባት ላይ የሚመሠረት እንደሆነም አብራርተዋል። ይህ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን አስተያየት የተሰማው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁለቱ ተዋጊዎች የንጹሐንን እልቂት እንዲያቆሙ ጫና እየደረሰባቸው ባለበት ወቅት ነው።
ከዚህ አስተያየት በተቃራኒ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ ትናንት ረቡዕ ‹‹ለእስራኤል ዜጎች ሰላምና ደኅንነት እስኪመለስ ድረስ ጥቃቱን እንቀጥልበታለን›› ብለዋል።
ሐሙስ ከቀትር በፊት ብቻ ከመቶ በላይ የእስራኤል የአየር ጥቃቶች በሐማስ ወታደራዊ መዋቅር ላይ እንደተተኮሱ ተዘግቧል። በምላሹ የፍልስጤም ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ሮኬት ተኩሰዋል።
አንድ የግብጽ የደኅንነት ምንጭ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ድርድሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ትናንት ረቡዕ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለ4ኛ ጊዜ ወደ ናታንያሁ ስልክ መተው በጉዳዩ ላይ ተወያይተዋል። ሁለቱን ወገኖች የማደራደር ሂደቱ አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ ዛሬ ጠዋት እስራኤል የአየር ጥቃት ማድረጓንም የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡
እስካሁን በነበረው ጦርነት በትንሹ 227 ፍልስጤማዊያን በጋዛ የተገደሉ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 100 የሚሆኑት ሕጻናትና ሴቶች ናቸው። በሌላ በኩል እስራኤል በኩል የሟቾቹ ቁጥር 12 ብቻ መሆኑ ተነግሯል፡፡