Sunday, November 24, 2024
spot_img

መንግሥት አዲስ የተግባቦት ሰነድ ወደ ሥራ ማስገባቱ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ግንቦት 12፣ 2013 ― መንግሥት መረጃን ለሕዝብ በማቅረብና ተአማኒ በመሆን ረገድ ያለብኝን ችግር ይፈታል ያለውን የተግባቦት ሰነድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱ ተነግሯል፡፡

በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት እንደተዘጋጀ የተነገረለት ‹‹የኢፌዴሪ የተግባቦት ሰነድ›› የሚል ሥያሜ የተሰጠው ሰነድ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት፣ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት ቅርብ በሆኑ ጋዜጠኞች፣ በመረጃና ደኅንነት ተቋሙና በክልል መስተዳድር አካላት ሐሳብ የተሰጠበት እንደሆነ በመግቢያው ላይ እንደሚያትት ዋዜማ ራድዮ ዘግቧል፡፡

መንግሥት ከለውጡ ማግሥት አንስቶ ያከናወናቸውንና እያከናወንኩ ነው የሚለውን በጎ ተግባር ሕዝቡ በሚገባ እንዲረዳና ድጋፍ እንዲሰጥ የማስቻል ግብ ያለው ሰነድ፣ እስካሁን በነበረው የመረጃ ፍሰት ከፍተኛ የሆነ የተቋማት የቅንጅት ችግር እንደነበረ የሚያመለክት ነው፡፡

ቀድሞ የነበረው የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መፍረሱ በመንግሥት የተግባብቦት ስራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩንም ሰነዱ ይገልጻል።

አዲስ የተዘረጋው አደረጃጀት በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት፣ የፌደራሉ መንግስት ተቋማትና መንግስታዊ መዋቅሮችን የሚመራ መሆኑም ተነግሮለታል፡፡

ሰነዱ እያንዳንዱ የመንግሥት ተቋም እንደየ ስፋቱ ተጠሪ የኮምኒኬሽን ግብረ ኃይል እንዲያቋቁም ያዛል የተባለ ሲሆን፣ የግብረ ኀይሉ እስከ ስድስት የሚደርሱ ንዑስ ቡድኖች ይኖሩታል። እነዚህ ቡድኖች ስትራተጂክ ኮሙኒኬሽንስ፣ የመገናኛ ብዙሀን ግንኙነት አስተባባሪ፣ የውጪ ግንኙነት፣ ዲጂታል ኮሙኒኬሽንስ፣ የውስጥ ግንኙነት እና የማኅበራዊ ቅስቀሳ ቡድን ተብለው የሚዋቀሩ ናቸው።

መንግሥታዊውን የመረጃ ፍሰት ለማቀናጀት ሲባል እያንዳንዱ መስሪያ ቤት የሁለት ሳምንት የስራ ዕቅዱን ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ልኮ ማስፀደቅ ይጠበቅበታል።

በተጨማሪም ‹‹የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት የሚያገኙ ከመንግስት የሚመጡ ማናቸውም ዜናዎች በእቅድ ሰነዱ ውስጥ መካተት እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ቀድመው መጋራት አለባቸው›› ሲል ይመክራል፡፡

የመረጃ ሰራተኞቹ በፊናቸው የሚኒስትሮች መልእክቶች፣ ንግግሮች፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎች እና ጉብኝቶች፣ ሚኒስትሮች የተሳተፉባቸው ቃለ ምልልሶች ወይም ርእሰ አንቀጾች፣ የመገናኛ ብዙሀን ሽፋን የሚያገኙ ስብሰባዎች፣ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ለጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት ያሳውቃሉ ።

ከመንግስት ተቋማት ውጪ ያሉ መረጃዎችንና ክንውኖችንም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተሰራ የስታትስቲክስ/መረጃ ልቀቶች፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተዘጋጁ ሪፖርቶች፣ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሚስቡ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን መከታተል የነዚሁ የመረጃ ግብረ ሀይል ሰራተኞች ድርሻ ነው።

በየተቋማቱ የሚወከሉ የመረጃ ኃላፊዎች አለቆቻቸው አልያም የሚመለከተው የክፍል ኃላፊ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ የሚያደርግ ከሆነ ጥያቄ ያቀረበው ሚዲያና ጋዜጠኛ፣ የውይይቱ ጭብጥ እንዲሁም በውይይቱ የተካፈሉ ሌሎች አካላት ካሉ በቅፅ ተዘርዝረው ሪፖርት ይደረጋሉ።

የማህበራዊ ሚዲያን አንገብጋቢ አስፈላጊነት ያብራራው የሰነዱ ክፍል ደግሞ ‹‹ክንውኖችን ለመከታተል፣ ልዩ ልዩ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እና ዋነኛ ተጽዕኖ አሳዳሪዎችን ለመለየት ያስችለናል፡፡ መደበኛ የዜና አውታሮችን ከሚከታተሉ ተተኳሪ አካላት ባለፈ መልእክቶቻችንን በቀጥታ በማድረስ ተጽዕኖ ለማሳደር ዕድልን ያመቻችልናል›› ሲል ይጀምራል።

የሕዝቡ የልብ ትርታ ምን እንደሆነ ለመገንዘብ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን ለመከታተል ማህበራዊ ሚዲያ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ይገልፅና ትኩረት ሳቢ እና ከተቋማችን ጋር ግንኙነት ያላቸውን ‘የሶስተኛ ወገን ይዘት’ ማጋራት ያለውን ጠቀሜታ ይጠቁማል።

‹‹ጥብቅ እና የተወሰኑ ሐላፊዎች ብቻ ሊያውቋቸው የሚገቡ መረጃዎችን ወይም ከወንጀለኛ፣ ከሽብርተኛ ወይም ከስለላ አካላት በእናንተ ወይም በባልደረቦቻችሁ ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ መረጃዎችን ይፋ አታውጡ›› ሲልም ይመክራል።

የመንግስት ባለስልጣናት እና ሲቪል ሰራተኞች ማህበራዊ ሚዲያ መጠቀም እንደማይከለከሉ ይሁንና የያዙትን ኃላፊነት የሚፃረርና የፖለቲካ ወገንተኝነትን የሚያንፀባርቅ መረጃ ከማጋራት እንዲቆጠቡ ይላል ይህ የመንግስት የተግባቦት ሰነድ።

መረጃዎች በከፍተኛ ባለስልጣናትና በየተቋሞቹ ማህበራዊ ገፆች ቢሰራጩ ጠቃሚ መሆኑን የሚያብራራው ሰነዱ፣ በቀውስ ግዜ የሚኖር የመረጃ ማቀናጀትና ማዕከላዊ በሆነ መንገድ መረጃን ማሰራጨት ተገቢ መሆም ሰፍሮበታል፡፡

ፎቶ፡ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ሥዩም

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img