አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 11፣ 2013 ― የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የግብፅ ፍላጎት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አንደማይኖረው የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ የተሌቪዥን ሾው ላይ ቀርበው የተናገሩት ሳሚ ሹክሪ፣ ግብፅ በአስዋን ግድብ ያላት የውሃ ክምችት መተማመን እንደፈጠራላት ነው የገለጹት፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ‹‹ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት የግብፅ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ እንደማይኖረው እንተማመናለን›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ግብፅ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት ጀምሮ ሙሌቱ የውሃ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል በሚል ሂደቱን ስትቃወም መሰንበቷ የሚታወቅ ነው፡፡
አሁንም ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት በተለያዩ መንገዶች እና ውይይቶች ተመሳሳይ ቅሬታ ስታቀርብ መቆየቷም ይታወሳል፡፡