አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ግንቦት 11፣ 2013 ― በቤንች ሸኮ ዞን በሸኮ ወረዳ በአይበራና ሳንቃ ቀበሌ ላይ በፀጥታ አካላት ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሦስት መደበኛ ፖሊሶች እና ስድስት ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ሌሎች ሦስት ደግሞ መቁሰላቸውን የቤንች ሸኮ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዳዊት ጢሞቲዎስ መግለጻቸውን የዞኑ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡
ኮማንደር ዳዊት በሰጡት መግለጫ ‹‹ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተከሠቱ የፀጥታ ችግሮችን በሸኮ ወረዳ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከሠላም አምባሳደሮች ጋር በተሠራው ስራ ችግሩ ከተከሰተበት ቀበሌ በስተቀር በወረዳው ላይ አንፃራዊ ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን›› ያነሱ ሲሆን፣ በአይበራና ሳንቃ እንዲሁም በርጊ ቀበሌ ‹‹ሠላምን ለማረጋገጥ የፀጥታ አካሉ ህብረተሠቡን አስተባብሮ ሥራ እየሰራ ባለበት ሁኔታ የተፈፀመው ጥቃት ማንንም የማይወክል የፀረ ሠላም ኃይሎች ተግባር ነው›› ብለውታል፡፡
ጨምረውም ‹‹ፀረ ሠላም›› ሲሉ የገለጹት ኃይል፣ ‹‹በሠላማዊው ሕዝብ ውስጥ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ አስተማሪ እርምጃ ለመውሰድ የመነጠል ስራውን ህዝቡን አሳትፎ እየተሠራ›› እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡