አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 10፣ 2013 ― ዋና መቀመጫው አሜሪካ ኒውዮርክ ያደረገው አሶሼትድ ኘረስ ከሦስት ቀናት በፊት የአገር አቀፉን ምርጫ በተመለከተ የሠራው ዘገባ ከእውነት የራቀ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
ኢቢሲ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ ምርጫው በግልጽ እና በአደባባይ ከሎጂስቲክስ አቅርቦት እና ከአጠቃላይ ስራ መጓተት ጋር ተያይዞ ለተወሰኑ ሳምንታት መራዘሙ እየታወቀ ምርጫው የተራዘመው በትግራይ ክልል ካለው ጦርነት ጋር በተገናኘ ነው ብሎ ከእውነት የራቀ ዘገባ ሰርቷል ማለታቸውን ዘግቧል፡፡
አሶሼትድ ኘረስ ይህንኑ ዘገባ መሥራቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ዋና ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በቀጣይም በኢትዮጵያ ፈቃድ አግኝተው በሚንቀሳቀሱ ነገር ግን ሕግ እና ሥርዓትን ተከትለው በማይሠሩ መገናኛ ብዙሃን ላይ መሰል እርምጃ እንደሚወሰድ አቶ መሐመድ በሰጡት መግለጫ አስጠንቅቀዋል።
አሶሴትድ ፕረስ ከበለሥልጣኑ ማስጠንቀቂያ ባስከተለበት ዘገባው በኢትዮጵያ ምርጫ በድጋሚ እንዲራዘም የተደረገው የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው አንሳተፍም ካሉ በኋላ እንዲሁም በትግራይ ክልል ባለው ግጭት ምክያት ክልሉ ላይ ምርጫ ስለማይካሄድ ነው የሚል አስነብቧል።
ሆኖም ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ቀን ማራዘም ያስፈለገበትን ምክያት ሲዘረዝር ያነሳቸው ጉዳዮች የድምፅ መስጫ ወረቀት ህትመት የወሰደው ጊዜ በመኖሩ፣ የመራጮች ምዝገባ የወሰደው ተጨማሪ ጊዜ በመኖሩ፣ ለቁሳቁስ ማጓጓዣ በቂ ጊዜ ስለሚያስፈልግ እና በአንድ ምርጫ ጣቢያ ሦስት የነበሩትን የምርጫ አስፈፃሚዎች መጨመር በማስፈለጉ የሚል ነበር፡፡