Thursday, November 21, 2024
spot_img

ምርጫ ቦርድ በሰበር ሰሚ ችሎት ላቀረበው ይግባኝ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ምላሽ ሰጠ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 9፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች የመምረጥ መብትን በተመለከተ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ላቀረበው ይግባኝ፤ የክልሉ ብሔራዊ ጉባኤ ዛሬ በፍርድ ቤት ምላሽ ሰጠ። ጉባኤው በምርጫ ቦርድ በኩል ለተነሱ የመከራከሪያ ነጥቦች ምላሽ የሚሆን ባለ 12 ገጽ መልስ ያቀረበው በችሎቱ ጽሕፈት ቤት በኩል ነው።

ምርጫ ቦርድ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያለው፤ ከክልሉ ውጪ ያሉ የሐረሪ ብሔር ተወላጆች ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ በአባልነት የሚወዳደሩ ግለሰቦችን የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት የምርጫ ሂደት ከዚህ ቀደም በነበሩ አምስት ተከታታይ ሀገራዊ ምርጫዎች ላይ ይደረግ በነበረው መልኩ እንዲፈጸምም ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ይህን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ የተቃወመው ምርጫ ቦርድ ለሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታውን ያስገባው ባለፈው ሳምንት ሰኞ ግንቦት 2፣ 2013 ነበር። ቦርዱ በይግባኙ ላይ፤ በጠቅላይ ፍርድ ቤት በተካሄደው ክርክር ወቅት የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ‹‹በልዩ ሁኔታ ስለሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ›› በአዋጅ የተደነገገውን በማንሳት መከራከሩን አስታውሷል።

በሐረሪ ክልል ሕገ መንግስት ላይ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ከክልሉ ውጪ ባሉ የብሔረሰቡ አባላት ጭምር እንዲመረጥ ማስቀመጡ እና ይህንንም ድንጋጌ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተቀብሎ ያለ ሥልጣኑ ሕገ መንግስትን መተርጎሙን ምርጫ ቦርድ በይግባኙ ላይ አመልክቷል። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚህ ድርጊቱ ‹‹ተደራራቢ የሕግ ጥሰት ፈፅሟል›› ያለው ምርጫ ቦርድ፤ የሰበር ሰሚ ችሎት ይህን የሕግ ጥሰት እንዲያርም ሲል አቤቱታውን አቅርቧል።

የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ለዚህ አቤቱታ በሰጠው ምላሽ፤ ምርጫ ቦርድ የፌደራል ህገ መንግስቱን ድንጋጌዎች ‹‹በተሳሳተ መልኩ ተርጉሞታል›› ብሏል። በፈደራሉ ሕገ መንግስት ላይ የተዘረዘሩ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ድንጋጌዎች በሙሉ የነዋሪነትን መስፈርት ባላቀመጡበት ሁኔታ፤ ህገ መንግስቱ በ‹‹ክልል ውስጥ (territorial) የሆነ መርህን ይከተላል ማለቱ አግባብነት የለውም›› ሲል ብሔራዊ ጉባኤው መከራከሪያውን አስቀምጧል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ የቀረበውን አጠቃላይ አቤቱታ ውድቅ በማድረግም የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ እንዲያጸና የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ በምላሽ ማጠቃለያው ላይ ጠይቋል።

የብሔራዊ ጉባኤውን ዝርዝር ምላሽ በጽሕፈት ቤት በኩል የተቀበለው ሰበር ሰሚ ችሎቱ፣ ምርጫ ቦርድ ለተነሱት መከራከሪያዎች የመልስ መልስ እንዲሰጥ ለነገ ረቡዕ ግንቦት 11 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ ገጽ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img