አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 9፣ 2013 ― መንግሥት ከህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተኩስ በማቆም ተደራደሩ በሚል የሚቀርቡ ምንም ዓይነት ግፊቶችን ፈጽሞ እንደማይቀበል ኢ ፍትሐዊ እና ያልተገቡ ክሶች እና ዘመቻዎች በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ነው ሲል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣው መግለጫው አሳውቋል።
መንግስት ምንም እንኳን በአጋሮቹ ለሚገለጹ ስጋቶች እና ለሚነሱ ጥያቄዎች ተባባሪ ሆኖ በቅንጅት ለመፍታት ያለውን ዝግጁነት ቢገልጽም፣ በእንዲህ ዓይነት ያልተገቡ ዘመቻዎች ኢትዮጵያን ከልክ ባለፈ ጫና ውስጥ ለማስገባት የሚደረገው ጥረት የሚያስቆጭ ነው ሲል የሚያትተው መግለጫው ዘመቻው ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ይበልጥ የሚያባብስ መሆኑን ገልጿል።
በትግራይ ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ ከመቻልም በዘለለ የአቅርቦት በሮች ሁሉ ተመቻችተዋል ያለው መንግሥት፣ ተፈጽመዋል የተባሉ ሰብዓዊ ጥሰቶች በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ፌዴራል ፖሊስ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጭምር መመርመራቸውን፤ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን አመልክቷል።
በተለይም ከፊቱ ምርጫ እንዳለበት ሃገር ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችሉ ውይይቶችን ከተለያዩ አካላት ጋር ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ነው መንግስት በመግለጫው የጠቆመው፡፡
ውይይቱን በትግራይ ክልል ጭምር ከህጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ አባላት፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራን፣ ከታዋቂ ግለሰቦች እና ከሌሎች አካላትም ጋር ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት ማሳየቱንም ነው ያስታወቀው፡፡
ሆኖም ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በዚህ ብሔራዊ የውይይት ሂደት እንዲካተት እና የውይይቱ አካል እንዲሆን የሚደረገው ግፊት ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡
ህወሓት የሃገሪቱን ሉዓላዊነት እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ህገወጥ ቡድን እንደሆነ ያስታወቀም ሲሆን በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት መፈረጁን አስታውሷል፡፡
ተኩሱ ቆሞ ተደራደሩ በሚል የሚቀርቡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ፈጽሞ የማይቀበለው በዚህ ምክንያት እንደሆነም ነው የገለጸው፡፡
በተቃዋሚዎች እና ጋዜጠኞች ላይ ያልተገቡ እርምጃዎችን ወስዷል በሚል የሚቀርቡ “መሰረተ ቢስ” ክሶች የመንግስትን ስም ከማጉደፍና የምርጫውን ሂደት ከማጣጣል ያለፈ ፋይዳ የላቸውምም ብሏል።
በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሃገራዊ የውስጥ ጉዳዮች ላይ በዋናነትም ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ተደጋጋሚ ጣልቃ ገብነቶች እንዳሉም መግለጫው አስታውሷል፡፡
ሆኖም ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሃገር እንደመሆኗ መጠን የውስጥ ጉዳዮቿን በተመለከተ ከውጭ የሚመጡ መመሪያዎችን ልትቀበል አትችልም ሲል አክሏል።
በሃገሪቱ አራቱም ማዕዘናት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አስፈላጊ እርምጃዎችን የመውሰዱ ኃላፊነት በብቸኝነት የመንግስት መሆኑንም የጠቆመ ሲሆን፣ ህግ እና ህገመንግስትን እንዲያስከብር በህገ መንግስቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻ ማካሄዱንም ገልጿል፡፡
በጋራ ጉዳዮች ላይ የመምከሩ ዝግጁነትና ፍላጎት የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን በማስታወስም በውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት ጫና ለማድረግ ከሚሞክሩ አጋሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነት በድጋሚ ለማጤን ሊገደድ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
በማይመለከተው የውስጥ ጉዳይ ላይ መስጋቱን ደጋግሞ የሚገልጽ አካል ኢትዮጵያ በግልጽ ተወራ እየተመለከተ ዝም ሊል እንደማይችልም ነው መግለጫው ያስቀመጠው፡፡
ተገቢ አይደሉም ያላቸውን መግለጫዎች መቀበል አይደለም ውድቅ የሚያደርገው በዚሁ ምክንያት እንደሆነም መንግሥት ገልጿል።