Sunday, September 22, 2024
spot_img

በምሥራቅ ወለጋ የነጋዴዎችና የአርሶ አደሮች ንብረት እየተዘረፈ መሆኑ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 9፣ 2013 ― በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ፣ ሊሙ ገሊላ እና ጊዳ አያና ወረዳ በነበረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች ከገጠር አከባቢዎች ያመረቱትን የሰብል እህል ጭነው ሲንቀሳቀሱ መዘረፋቸው ተነግሯል፡፡

በሁለቱ ወረዳዎች ከዚህ በፊት በነበረው የጸጥታ ችግር ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች፣ ትተውት የሸሹትን እህል ጭነው አሁን ላይ ወደሚኖሩበት አካባቢ በማጓጓዝ ላይ እያሉ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መለዮ በለበሱ ግለሰቦች ተዘርፈናል ሲሉ ነው ቅሬታቸውን የገለጹት። ከአርሶ አደሮች እህል ገዝተው ወደ ከተማ ለንግድ በማጓጓዝ ላይ ያሉ ነጋዴዎችም እስከ መኪናው ንብረታቸውን እንደተቀሙ ተናግረዋል።

ከገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ በመጓጓዝ ላይ በነበሩ ተሽከርካሪዎች የጫኑትን እህል ጨምሮ በመንገድ ላይ የታገቱትና የተወሰደባቸው፣ የክልሉን ልዩ ኃይል መለዮ በለበሱ ግለሰቦች ‹‹ሕገ ወጥ እና የተዘረፈ ንብረት ነው›› በሚል ሰበብ መሆኑን አርሶ አደሮቹና ነጋዴዎቹ ጠቁመዋል።

የነጋዴዎችና የአርሶ አደሮችን እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎች እህሉን ዘርፈዋል ብለው ካገቱት አካላት የብር ክፈሉ ጥያቄ እንደቀረበላቸውም ጠቁመዋል። ከታገቱት ተሽከርካሪዎች መካከል የአንዱ ሹፌር ብር ከፍሎ እህሉንም መኪናውንም መውሰድ እንደሚችል ተነግሮት ብር ቢከፍልም መኪናውና እህሉንም ማግኘት እንዳልቻለ ተሰምቷል፡፡

በዚህም ሹፌሮችና ነጋዴዎች ለህይዎታቸው በመስጋት ንብረታቸውን ከእነመኪናው ትተው ለመሸሽ እንደተገደዱ ጠቁመዋል።

በሕገወጥ ሰበብ የተወሰደን የነጋዴዎችና የአርሶ አደሮችን ንብረት ለማስመለስ በተለይ ነጋደዎች የንግድ ፈቃዳቸውንና የገዙበትን ማስረጃ ቢያቀርቡም ንብረታቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የገለጹት።

ከአርሶ አደሮቹ ሰምቻለሁ ብሎ አዲስ ማለዳ እንደዘገበው በተፈጠረው ችግር ጥለውት የሸሹትን እህል ለመጫን የተገደዱት በአቅራቢያው ከሚገኙ አከባቢዎች በሚወጡ ግለሰቦች ንብረታቸው እየተወሰደ በመሆኑ ነው።

ከገጠር ቀበሌዎች በመጓጓዝ ላይ እያለ ተዘርፏል የተባለው እህል መጠን እስከ 800 ኩንታል እንደሚደርስ ተጠቁሟል። አርሶ አደሮች ያመረቱትን፣ ነጋዴዎች ከገበሬዎች የገዙትን እህል መነጠቃቸውንና ፍትሕ ማጣታቸውን በመግለጽ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ችግራቸውን ተረድቶ በአስቸኳይ ንብረታቸውን እንዲያስመልስላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ የቀረበውን ጥያቄ እንደሚያጣሩና ችግሩን እንደሚፈታ ነው የተነገረው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img