Saturday, September 21, 2024
spot_img

ደቡብ ግሎባል ባንክ እና አዋሽ ኢንሹራንስ ከወለድ ነጻ አገልግሎትን ተቀላቀሉ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 9፣ 2013 ― ደቡብ ግሎባል ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመጀመር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘቱን ሲገልጽ፣ አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ደግሞ ከወለድ ነጻ የኢንሹራንስ አገልግሎት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ደቡብ ግሎባል ባንክ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ማግኘቱን አስመልክቶ በወጣው መግለጫ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመቀበሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ በመግባት በተመረጡ ቅርንጫፎቹ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስኮቶችን በመመደብ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማና በክልል አንዳንድ ከተሞች ከወለድ ነፃ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ስለማቀዱም ገልጿል፡፡

እንደ ባንኩ መግለጫ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡት ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ የተጠቃሚዎችን በተለይም የእስልምና እምነት ተከታዮችን ምቾት የጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችል አቅርቦት ያሟሉ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

ደቡብ ግሎባል ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሲጀምር በዋናነት እንደሚተገብራቸው የገለጻቸው የአገልግሎት ዓይነቶቹ የዋዲያና የኢንቨስትመንት ተቀማጭ ሒሳብ የፋይናንስ ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት፣ የውጭ ምንዛሪ የተለያዩ የባንክ ዋስትናና የገንዘብ ማስተላለፍ (ሐዋላ) አገልግሎት ናቸው፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች በየዘርፋቸው በርካታ ልዩ ልዩ ዓይነት አገልግሎት እንደያዙም ጠቅሷል፡፡

በተያያዘ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ አገልግሎት ‹‹ታካፉል›› ኢንሹራንስ ለመስጠት ፈቃድ ከጠየቁ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው አዋሽ ኢንሹራንስ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

እንደ ባንክ አገልግሎት ሁሉ የሸሪዓ ሕግን ተከትሎ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት የሚያስችለውና ታካፉል የተባለውን አገልግሎት ለመጀመር ፈቃድ ያገኘው አዋሽ ኢንሹራንስ፣ አገልግሎቱን ይህ በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት በተመረጡ ቅርንጫፎች በመስኮት ደረጃ ሥራ አስጀምራለሁ ብሏል፡፡

ኩባንያው ታካፉልን መጀመሩ የመድን ሽፋንን ከማስፋት አኳያ እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የሚያመላክተው የአዋሽ ኢንሹራንስ መረጃ፣ በእምነታቸው ምክንያት የመድን አገልግሎት ያላገኙ ወገኖችንም በመድረስ የአገልግሎት ተጠቃሚዎችን እንደሚያሰፋ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመስኮት ደረጃ የታካፉል ኢንሹራንስ አገልግሎትን ለመጀመር ከስምንት በላይ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየጠበቁ መሆኑን የዘገበው ሪፖርተር ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img