አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 7፣ 2013 ― በማዕድን ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ ወስደው የልማት እንቅስቃሴያቸው ችግር እንዳለበት የተለዩ የ27 ኩባንያዎች ፈቃድ መሠረዙን የማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር አስታውቋል፡፡
ሚንስቴሩ እንደገለጸው ፈቃዳቸው የተሰረዘው 27 ተቋማት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በማዕድን ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ ቢወስዱም በተደረገባቸው ማጣራት የማልማት ስራውን በተጓተተ መልኩ እያከናወኑ በመሆኑ፣ ቃል የገቡትን ውጤት ማስመዝገብ ባለመቻላቸውና ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባት ባለመቻላቸው ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ምክንያት ሆኗል።
ከጥቂት ወራት በፊት በተደረገ ማጣራት ከላይ የተገለጹት ችግሮች የታዩባቸው 63 ተቋማት የማዕድን ልማት ፈቃድ መሠረዙ ይታወሳል።
የማዕድን የሀብት ብክነት በዝምታ የሚታለፍ እንቀዳልሆነ በመጠቆም በቀጣይም ተመሳሳይ የማጣራት ስራ በማከናወን ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ እንደሚቀጥል የገለጸው ሚንስቴሩ፤ ፍቃዳቸው በተሰረዘ ተቋማት ተይዘው የነበሩ የማዕድን ቦታዎችም ግልጽ በሆነ ዓለም አቀፍ ጨረታ በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ማስታወቁን የዘገበው ሪፖርተር ነው፡፡