አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 5፣ 2013 ― የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ትገኝበታለች ካሉት ‹‹መስቀለኛ መንገድ›› ወጥታ ወደ ሰላማዊ፣ የተረጋጋ እና ዴሞክራሲ እንድትሸጋገር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲደርግ ጠይቀዋል፡፡
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ይህንኑ ጥያቄያቸውን ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ መጥተው ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር ለመከሩት አሜሪካ ለምሥራቅ አፍሪካ ችግሮች መፍትሔ እንዲያመጡ ለሾመቻቸው ጄፍሪ ፌልትማን በጻፉት ደብዳቤ አስፍረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ባሰፈሩበት ዘለግ ያለ ደብዳቤያቸው፣ ፓርቲያቸው ለምን በምርጫ እንዳልተሳተፈ ከማብራራት አንስቶ በአገሪቱ በቀጣይ የተሻለ ሁኔታ እንዲኖር ቢደረጉ ያሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦችም ሰንዝረዋል፡፡
መፍትሔ ይሆናል ብለው ካሰፈሩት መካከል መንግሥት ምርጫውን አቁሞ ሁሉን ዐቀፍ ንግግር እንዲደረግ፣ የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈታ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ ይፈጽማቸዋል ያሏቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲያቆም እንዲደረግ መጠየቃቸው ይገኝበታል፡፡
በሌላ በኩል ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ደብዳቤ የተዉላቸው አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥሩ አቀባበል እንዳልገጠማቸው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡