አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 5፣ 2013 ― የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን የኒውዮርክ ታይምስን የኢትዮጵያ ሪፖርተር ፍቃድ መሰረዙን ከራሱ ከጋዜጣው እና ከባለሥልጣኑ አረጋግጫለሁ ብሎ ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
በባለሥልጣኑ ፍቃዱን የተቀማው አየርላንዳዊ ዜግነት ያለው ሳይመን ማርከስ የተባለ ጋዜጠኛ ሲሆን፣ ፍቃዱ የተሰረዘው ትግራይ ክልል ደርሶ ከጦርነቱ የተረፉ ሰዎችን አነጋግሮ ሲመለስ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የጋዜጠኛው ፍቃድ የተሰረዘው ባለፈው ወር መሆኑን ያስታወሰው ቀጣሪው ኒውዮርክ ታይምስ፣ የሚያበሳጭ ያለው ውሳኔ እንዲቀለበስ ለአዲሶቹ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም ለውጥ እንደሌለ አሳውቋል፡፡
ሬውተርስ ጉዳዩን አስመልክቶ አዲሱን የባለሥልጣኑን አለቃ አቶ መሐመድ ኢድሪስን ጠይቄ የቀድሞዎቹ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች የጋዜጠኛውን ፍቃድ የሰረዙት ‹‹ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ›› በማቅረቡ መሆኑን ገልጸውልኛል ብሏል፡፡
ጋዜጠኛው ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታለት መጠየቁን ጨምረው የገለጹት አቶ መሐመድ፣ ሆኖም በተያዘው ወር በሚካሄደው ምርጫ ሰበብ በሌሎች ጉዳዮች ስለተወጠሩ መመልከት አልቻልንም ብለዋል፡፡
አክለውም በትልቁ ምስል ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ ያነሱት አቶ መሐመድ፣ ከኒውዮርክ ታይምስም ጋር ሆነ ከሌላ ሚዲያ ጋር ችግር እንደሌለባቸው በመጠቆም ይህ ጉዳይ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡