Monday, November 25, 2024
spot_img

በዐቃቤ ሕግ የወጣው የአክሱም ሪፖርት ከሒዩማን ራይትስ ዎች ነቀፌታ አስተናገደ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ግንቦት 5፣ 2013 ― የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከቀናት በፊት በአክሱም ከተማ በሕዳር ወር የነበረውን ግጭት አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት የሞቱ ሰዎች ንጹሐን ሳይሆኑ ከኤርትራ ወታደሮች ጋር ጦርነት የገጠሙ ታጣቂዎች ናቸው ማለቱ የንጹሐን ነፍስ መቀጠፉን የካደ ነው በሚል ከሒዩማን ራይትስ ዎች ነቀፌታን አስተናግዷል፡፡

የመብት ተሟጋቹ በአክሱም የተፈጠረውን ክስተት አስመልክቶ አገኝቼዋለሁ ባለው መረጃ በከተማው ማይ ኩሆ በተባለ ተራራ አካባቢ ወጣቶችና ጥቂት ታጣቂ ሰዎች ከትግራይ ሚኒሻ ጋር በማበር የኤርትራ ወታደሮችን የገጠሙ ቢሆንም፣ የኤርትራ ወታደሮች በአጸፋው ኅዳር 19 እና 20 በንጹሐን ላይ ጭምር ጭፍጨፋ መፈጸማቸውን ገልጾ ነበር፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የኤርትራ ወታደሮች በከተማው በ24 ሰኣት ውስጥ ያደረሱትን ይህን በተለይ ወጣት ወንዶች ላይ አተኩሯል ያለውን ግድያ የካደ ነው ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ የመንግሥት አካል የሆነው ዐቃቤ ሕግ ይህን መረጃ መዝለሉ በክልሉ የተፈጸመው ጥቃት በገለልተኛ አካል ሊጣራ እንደሚገባው አመልካች መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በኅዳር ወር የኤርትራ ወታደሮች በፈጸሙት ጭፍጨፋ ከ200 በላይ ሰዎችን መግደላቸውን ሌላኛው የመብት ተሟጋች ድርጅት አምኔስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት አመልክቶ ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img