አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 3፣ 2013 ― ስድስተኛውን አገር ዐቀፍ ምርጫ ለማካሄድ በአዲስ አበባና በድሬድዋ ከተማ አስተዳደር የድምጽ መስጫ ቀን ወደ አገራዊ ድምጽ መስጫ ቀን እንዲመለስ ባልደራስ፣ እናት ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሚገኙበት ስብስብ ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ጥያቄ አቀረበ፡፡
በኢትዮጵያ በተያዘው ወር አገር ዐቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ አገራዊ ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 28፣ 2013 ሲሆን፣ የአዲስ አበባና የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የድምጽ መስጫ ቀን በሳምንቱ ሰኔ 5፣2013 መሆኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ምርጫ በሁለት የተለያየ ቀን መደረግ የለበትም የሚል ጥያቄ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ተነስቷል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበው ጥያቄ የአዲስ አበባና ድሬድዋ ከተማ አስተዳደር የድምጽ መስጫ ቀን አንድ ላይ እንዲሆን ፓርቲዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን በደብዳቤ እንዲያቀርቡና ጉዳዩ ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ባቀረቡት ሐሳብ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
ፓርቲዎቹ ደብዳቤያቸውን አስገብተው ምላሹን እየተጠባበቁአ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን፣ በምርጫ ቦርድ በኩል እስካሁን የተሰጠ መልስ የለም፡፡