Monday, September 23, 2024
spot_img

በኮቪድ ሰበብ የቀብር ማስፈፀሚያ ዋጋ መወደዱ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ግንቦት 3፣ 2013 ― በኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በሟቾች ቁጥር መበራከት የሬሳ ሳጥን፣ የቀብር አስፈጻሚ ትራንስፖርት አገልግሎት እና የቀብር ቦታዎች ዋጋ በመወደዱ መቸገራቸውን አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የዕድር ኃላፊዎች ነግረውኛል ብሎ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ብዙ የአካባቢዎቻችንን ሰዎች እያጡ መሆናቸውን የገለጹ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በዚህ ቫይረስም ሆነ በሌሎች በሽታዎች ወይም አደጋ የሚሞተውን ሰው ቀብር ለማስፈፀም የሚያስፈልገው ወጪ ደግሞ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል አቅም እየተፈታተነ ነው ብለዋል፡፡

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅቶች እና የሬሳ ሳጥን ሻጮች በበኩላቸዉ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ቀብር አስፈጻሚ ድርጅት አንዱ የሆነው አቤኔዘር ቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የመኪና ሰርቪስ ማድረጊያውና የነዳጅ ዋጋ ቢጨምርም፣ በአገልግሎቱ ላይ የተጨመር ዋጋ የለም ያሉ ሲሆን፤ ነገር ግን አሁን ላይ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከሚሞተው ሰው ጋር ተያይዞ የቀብር ሰአት መደራረብ በአገልግሎታቸዉ ላይ ችግር እየፈጠረባቸዉ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ ለቀብር ስርዓት ከ2 ሺሕ እስከ 5 ሺሕ ብር ድረስ፣ የዲኮርና አበባ ዋጋን ጨምሮ፣ በየደረጃው የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ አክለውም የሬሳ ሳጥን ዋጋ የጨመረው ሕብረተሰቡ እንደሚለው ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከሠራተኛ እና ከቁሳቁስ ዋጋ መጨመር ጋር የተያያዠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ከሆነ አሁን ላይ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ሬሳ ተሸካሚዎቻችን በአንድ ቀብር ለአንድ ሰው 150 ብር ይከፈላቸው የነበረ ሲሆን፣ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተና ሰዉ መሞት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግን ለተሸካሚ በነፍስ ወከፍ 400 ብር አድጓል፡፡

ከቀብር ቦታ ጋር በተያያዘ አስተያየት የሠጡ የተለያዩ የእምነት ተቋማት አስተዳዳሪዎች እንደገለፀት፣ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የመሬት ላይ ቀብር እንደሌላቸዉ እና በተለምዶ ፉካ በመባል የሚታወቁት በማኅበር የሚሰሩ የቀብር ቤቶች (ኪስ) ብቻ ያላቸዉ እና የደብሩ( የአካባቢውን) ሰው ብቻ የሚያስተናግዱም መሆናቸውን ጋዜጣው በሥፍራዎቹ በመገኘት ካሰባሰብኩት መረጃ ተረድቻለሁ ብሏል፡፡

የመሬት ቀብር በሌለባቸዉ ቤተ እምነቶች አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችም እንደገለፁት ፉካዉ ከ30 እስከ 80 ሺሕ ብር የሚደርስ ዋጋ መጠየቁ ብቻ ሳይሆን የተገነቡት የማኅበር ቀብር ቤቶች (ፉካዎች) እጥረት እንዳለም አስታውቀዋል። የመሬት ላይ የመቃብር ቦታዎች እየተጣበቡ መምጣታቸዉ እና ያሉትም ቦታዎች ላይ ቀብር ለመፈጸም ሲሄዱ የቦታ መጣበብ እና የዋጋ ውድነት መኖሩ ተገልጧል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img