አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 2፣ 2013 ― የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማትያስ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሚያዝያ 30፣ 2013 በተለቀቀ ቪድዮ ላይ ያስተላለፉትን መልእክት ነቅፈው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ንግግሩን እንደሰሙ ወደ አማካሪቸው ደውለው ‹‹የተፈጠረውን ጉዳይ ለማጣራት›› መሞከራቸውን የገለጹት አቡነ ፋኑኤል፣ ‹‹የሃይማኖት መሪ የሚያደርገውን ንግግር ይዘትና ውጤት በደምብ መመዘን›› እንዳለበት በመጠቆም ‹‹የትግራይ ሕዝብ እንዲጠፋ ሞት ታውጆበታል ብለው መናገራቸው ጆሮን ጭው የሚያደርግና አስደንጋጭ ነው›› ብለውታል፡፡
በአቡነ ማትያስ ንግግር ሰበብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹ወደ እርስ በእርስ ግድያ ይገባ›› እንደነበር የገለጹት አቡነ ፋኑኤል፣ ሆኖም ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ ስለሆነ›› ይህ ሳይከሰት ቀርቷል ብለዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሠራዊት በተኛበት ሲታረድ፣ በማይካድራ አማራ ሲጨፈጨፍ፣ በመተከልና በአጣየ አማራ ሲገደል፣ በወለጋና በሻሸመኔ አማራ ሲገደል›› ዝም ብለዋል በማለትም አሁን አቡነ ማትያስ ስለ ትግራይ መናገራቸውን ተችተዋል፡፡
በሌላ በኩል ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ሊቀ ጳጳሱ ይህን የተናገሩት በአገሪቱ ‹‹ዲሞክራሲያዊ ለውጦች በመምጣታቸው ነው›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ኢትዮጵያ በለውጥ፣ በእድገት፣ በልማት ጎዳና ነው ላይ ያለችው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በትግራይ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተም ‹‹እርቅ እምቢ ያለው ሕወሐት ነው፣ መንግሥትማ የኮቪድ ማስክ እንጂ ጥይት መላክ አይፈልግም›› ሲሉ አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትን መሪ የሆኑት ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቅዳሜ እለት በእጅ ስልክ ተቀርጾ በተላለፈ የ14 ደቂቃ የቪድዮ መልእክታቸው፣ በትግራይ ክልል ተፈጽሟል ያሉትን ግድያ ያወገዙ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ቀደም ቢናገሩም እንደታፈነባቸው መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡ የአቡነ ማትያስ ቪድዮ መለቀቁን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ርእሰ ጉዳዩን ሲቀባበሉት ተስተውለዋል፡፡