Sunday, October 6, 2024
spot_img

በኦሮሚያ ክልል እስረኞች ተገደው የጦር መሣሪያ በመታጠቅ በሰው ሠራሽ ፀጉር ቪዲዮ እንደሚቀረፁ ኢሰመኮ አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 2፣ 2013 ― በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች የታሰሩ ሰዎች ተገደው ወታደራዊ ዩኒፎርም በመልበስና መሣሪያ በመታጠቅ ቪዲዮ እንደሚቀረፁ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጻቸውን ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ አክሎም በኦሮሚያ ክልል ክትትል ባደረገባቸው የተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎች ‹‹የኦነግ ሸኔ›› አባል ወይም ደጋፊ ‹‹ልጆቻችሁን አቅርቡ›› ተብለው እናቶችን የማሰር፣ በተመሳሳይም ‹‹ባልሽን አቅርቢ›› በማለት ሚስትን የማሰር ድርጊት እንደሚፈጸም፣ ከተለያዩ ታሳሪዎች አሳማኝ ምስክርነቶችን እንደተቀበለ ሚያዚያ 28፣ 2013 ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት አመልክቷል፡፡

ኮሚሽኑ ክትትል ካደረገባቸው የፖሊስ ጣቢያዎች መካከል በሦስቱ ማለትም በገደብ አሳሳ፣ በዶዶላና በአዳባ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የነበሩ በድምሩ አሥር ተጠርጣሪዎች ያለ ፍላጎታቸው ወደ ሻሸመኔ ከተማ ተወስደው የተፈጸመውን ጥሰት በሪፖርቱ አስፍሯል።

ከተገለጹት የፖሊስ ጣቢያዎች በድምሩ አሥር ተጠርጣሪዎች ያለ ፍላጎታቸው ወደ ሻሸመኔ ከተማ ከተወሰዱ በኋላ፣ ‹‹የታጣቂ ወይም የወታደር ልብስ እንዲለብሱ፣ አርቲፊሻል ፀጉር እንዲያደርጉና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን እንዲይዙ ተደርገው፣ ከዚያ በፊት ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር በቪዲዮ ካሜራ መቀረፃቸውን ለኮሚሽኑ ተናግረዋል፤›› በማለት በሪፖርቱ ይገልጻል።

ይህንን ቅሬታ በተመለከተ ስለሁኔታው የሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች ኃላፊዎች በኮሚሽኑ የክትትል ቡድን ተጠይቀው እስረኞቹ ወደ ሻሸመኔ መወሰዳቸውን ያረጋገጡ ቢሆንም፣ በካሜራ ስለመቀረፃቸው እንደማያውቁ መናገራቸውን ሪፖርቱ ይጠቅሳል።

የአንድ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ደግሞ ተጠርጣሪዎቹ ቪዲዮ መቀረፃቸውን ያመኑ ቢሆንም፣ የተቀረፁት ግን የጦር መሣሪያ በመያዝ ሳይሆን፣ ቀደም ሲል በሌላ ቦታ ወንጀል ፈጽመው አሁን ወደሚገኙበት ወረዳ የመጡ በመሆናቸው በፊት ከነበሩበት ወረዳ ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ በማገናኘት መረጃ ለመሰብሰብ እንደሆነ መግለጻቸውን ያትታል።

የኮሚሽኑ የክትትል ቡድን በተወሰኑ ቦታዎች ‹‹የኦነግ ሸኔ›› አባል ወይም ደጋፊ በመሆናቸው በሕግ እንደሚፈለጉ በመግለጽ፣ ‹‹ልጆቻችሁን አቅርቡ›› የተባሉ እናቶችና አባት ታስረው ማግኘታቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል።

በተመሳሳይ የኦነግ ሸኔ አባል ነው በማለት ‹‹ባልሽን አቅርቢ›› የተባለች የተጠርጣሪ ባለቤት መታሰሯንና መሰል ተገቢ ያልሆነ ሰዎችን የማሰር ድርጊት እንደሚፈጸም፣ ከተለያዩ ታሳሪዎች አሳማኝ ምስክርነቶችን እንደተቀበለ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይህንን ጉዳይ በማስመልከት በሰጠው ምላሽ ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚያስችል ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት መኖሩን በማመልከት፣ ቅሬታው ‹‹ከእውነት የራቀ›› እንደሆነና ያም ሆኖ ቅሬታዎቹ በማስረጃ ተደግፈው ከቀረቡ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለሕግ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ለኮሚሽኑ መግለጹን ሪፖርቱ ይጠቁማል።

የሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ በክልሉ ያለው የእስረኞች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አፋጣኝ መፍትሔ የሚያሻ ነው ብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img