አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 2፣ 2013 ― የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
በዚህ ወቅት ከፖለቲካው ዓለም ራሳቸውን የማግለል እቅድ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት ከእስር ሲፈቱ ከፖለቲካ ራሳቸውን ማግለል ይፈልጉ እንደነበር መናገራቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ በዚህ ወቅት ይህ ሐሳብ እንዳላቸው ጠይቄ ‹‹ከፖለቲካ ለመውጣት ተስፋ መቁረጥ አለብህ፤ ሁለተኛ ደግሞ በቃኝ ከዚህ በኋላ ምንም ትልቅ ለውጥ ማምጣት አልችልም የምትል እና ወደ ሌላ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ የሚል ደረጃ ላይ መድረስ አለብህ፤ አሁን ሳየው እዚያ ደረጃ ላይ መድረስ አልቻልኩም›› የሚል መልስ እንደሰጡት አስነብቧል፡፡
‹‹የዚህች አገር ትግል መሃል መንገድ ላይ ነው›› ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ ‹‹ወንዝ አልተሻገረም፤ አሁን የምንለያይበት ጊዜ አይደለም›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ተጨማሪም በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸው ፓርቲያቸውም ለኦሮሚያ ክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ መልካም አስተዋጽኦ ሲያበረክት እንደነበረ ፕሮፌሰር መረራ ተናግረው፣ ‹‹እንደ ታጋይ ምንም አልልም፤ ይህን ያህል ዓመት በትግል ውስጥ የቆየሁበትን ጊዜ ሳስበው የሚቆጨኝ ነገር የለም። ለምን ይህን ያህል ዓመት ትግል ውስጥ ቆየሁ ብዬ ሳስብ የሚቆጨኝ ነገር የለም፤ የቻልኩትን ያህል ሳበረክት ነው እስካሁን የመጣሁት›› ብለዋል፡፡
የኦፌኮ ሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ከተሳተፉበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በፖለቲካ ውስጥ ጎልህ ድርሻ አላቸው፡፡