Sunday, September 22, 2024
spot_img

ከመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን የሠላም አስከባሪ ኃይል አባላት በሱዳን ጥገኝነት መጠየቃቸውን ተመድ አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 2፣ 2013 ― በሱዳን የነበራቸውን ግዳጅ የጨረሱ 120 ኢትዮጵያውያን የሠላም አስከባሪ ኃይል አባላት ወደ አገራችን አንመለስም ብለው ዓለም አቀፍ ጥበቃ እና በሱዳን ጥገኝነት መጠየቃቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

የሠላም አስከባሪ አባላቱ በቅርቡ በተጠናቀቀው የተባበሩት መንግስታት የዳርፉር ተልዕኮ አካል የነበሩ ናቸው፡፡

ወታደሮቹ ወደ አገር ቤት አንመልስም ለማለታቸው በይፋ የተነገረ ነገር ባይኖርም፣ በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከሰቱት ውጥረቶች ጋር የተቆራኘ ሳይሆን አይቀርም መባሉን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

አሶሽየትድ ፕሬስ በበኩሉ ወደ አገራችን አንመለስም ካሉ የሠላም አስከባሪ ኃይል አባላት መካከል ከ30 በላይ የሚሆኑት ወደ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መግባታቸውን የሱዳን ባለሥልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል።

የሰሜን ዳርፉር ግዛት የስደተኞች ድርጅት ኃላፊ የሆኑት አል ፋቲህ ኢብራሂም መሐመድ ወደ ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

የስደተኞች ድርጅት ኃላፊው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ክስ ይጠብቀናል በሚል ፍራቻ ለመመለስ ፈቃደኛ ካልሆኑት መካከል 14ቱ ሴት የሠላም አስከባሪ አባላት ናቸው ብለዋል።

በተመሳሳይ ከወራት በፊት 15 በደቡብ ሱዳን የነበራቸውን ግዳጅ የጨረሱ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሠላም አስከባሪ ኃይል አባላት ወደ ኢትዮጵያ አንመለስም ማለታቸው ይታወሳል። አሁን ላይ ወደ አገራችን አንመለስም ያሉት 120 የሠላም አስከባሪ ኃይል አባላት የትግራይ ተወላጆች ስለመሆናቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ያለው ነገር የለም።

በተጨማሪም 31 ሌሎች የሠላም አስከባሪ ኃይሎች በዛሬው እለት ከሰሜን ዳርፉር ይወጣሉ የተባለ ሲሆን፣ እነዚህ የሠላም አስከባሪ ኃይሎች ከትግራይ ግጭት ሸሽተው ወደ ጎረቤት ሱዳን የተሰደዱ በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እንደሚቀላቀሉም ተነግሯል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img