Sunday, September 22, 2024
spot_img

ከትግራይ ክልል የተፈናቀሉ አንድ ሚሊዮን ያህል ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ሊመለሱ ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ግንቦት 2፣ 2013 ― በትግራይ ክልል በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የተፈናቀሉ አንድ ሚሊዮን ያህል ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ አስታውቀዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራው ዓለም አቀፍ ሕግጋት የሆኑትን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ፣ ክብርን የጠበቀ፣ በቂ ዝግጅት የተደረገበት፣ የደኅንነት ሥጋት የሌለበትና ዘላቂነት ያለው ይሆናል ብለዋል፡፡

በክልሉ በ12 መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት ተፈናቃዮች ሙሉ ሰላም ወደ ተረጋገጠባቸው ሥፍራዎች ሲመለሱ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እንደሚደረጉ፣ ሙሉ ሰላም ባልተረጋገጠባቸው ቦታዎች መመለስ ለማይችሉት ዘመድ ዘንድ ተጠግተው እንዲኖሩ የማመቻቸት፣ በሁለቱ መንገድ ከጣቢያዎቹ ሊወጡ የማይችሉ ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያ የሚቆዩ መሆኑንም ኮሚሽነር ምትኩ ተናግረዋል፡፡

ወደ ቀዬአቸው መመለስ ለማይችሉት በመቀሌ የካምፕ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነር ምትኩ፣ በቀጣይም በሽሬና በሌሎች ከተሞችም ይሠራል ብለዋል፡፡

ዝናብ ከመምጣቱ በፊት ተፈናቃዮች ተመልሰው ወደ እርሻ ሥራ እንዲገቡ፣ ቤተ ዘመድ ጋ የሚሄዱት ደግሞ እንዲሄዱና ወደ ሁለቱም መመለስ የማይችሉት በመጠለያ እንዲቆዩ ለማድረግ ከፍተኛ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ስለሚያስፈልጉ ይህንን ለማሟላት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ቅቱ የዝናብና ከ90 በመቶ በላይ የግብርና ምርት የሚገኘው በክረምት ከሚዘራው በመሆኑ የግብርና ሚኒስቴር ከ126 ሺሕ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ከጂቡቲ ወደብ እያጓጓዘ መሆኑን፣ ተጠቃሚ አርሶ አደሮችና በሰብል የሚሸፈነው መሬት መለየቱን፣ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ 5 ሺሕ 580 ኩንታል ያህል የምርጥ ዘር አቅርቦት እየተዘጋጀ መሆኑንና እያንዳንዱ አርሶ አደር በ2014 ተረጂ እንዳይሆን ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጠናቀቀ በኋላ በአንደኛው ዙር ለ4.5 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ መሠራጨቱን፣ በሁለተኛው ዙር ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ዕርዳታው እንዲደርሳቸው መደረጉንና ለሁለቱ ዙሮች ዕርዳታም 3.7 ቢሊዮን ብር ወይም 94.6 ሚሊዮን ዶላር እንደወጣ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የዕርዳታ አሸፋፈኑ 70 በመቶ በኢትዮጵያ መንግሥት፣ 27 በመቶ በዩኤስኤአይዲ ድጋፍ የሚደረግለት አገር በቀሉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሬስት፣ እንዲሁም ሦስት በመቶ በዓለም ምግብ ፕሮግራም የተሸፈነ መሆኑን፣ ለሦስተኛው ዙር ዕርዳታ ግን የአካሄድ ለውጥ ተደርጓል መባሉን የዘገበው ሪፖርተር ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img