አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 30፣ 2013 ― በነገው እለት ማለትም እሑድ ግንቦት 1፣ 2013 በመስቀል አደባባይ እንዲካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ‹‹ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር›› በታቀደው መሠረት እንደሚቀጥል አዘጋጆቹ ዛሬ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የዝግጅቱ አሰናጆች የሆኑት ‹‹ሐላል ፕሮሞሽን›› እና ‹‹ነጃሺ በጎ አድራጎት ድርጅት›› በመግለጫቸው ሺሕዎች ይሳተፉበታል ባሉት ኢፍጣር፣ በግብጽ ተይዞ የሚገኘው የሰባት ሺሕ ሰው ሪከርድ ይሻሻላል የሚል አላማ ማንገባቸውን ገልጸዋል፡፡
አዘጋጆቹ በመግለጫቸው የታሰቡትን አላማዎችን ለማሳካት ማንኛውም ፕሮግራሙን ለመታደም የሚመጣ ግለሰብ ለፀጥታ አካላት ለፍተሻ ከመተባበር ባለፈ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከሕጋዊ የአገሪቱ ሰንደቅ አላማ ውጭ ይዞ መምጣት እንደማይፈቀድ እንዲሁም ‹‹ተንኳሽና ሌሎች ወገኖቻችንን ሊያስከፋ የሚችል ምንም አይነት ጥቅስ መያዝ ፈፅሞ የተከለከለ›› መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡
በነገው እለት ከሚካሄደው የመስቀል አደባባይ ኢፍጣር ጋር በተገናኘ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ተቃውሞ የጻፈው ደብዳቤ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በሥፋት መነጋገሪያ ሆኖ አልፏል፡፡