Monday, October 7, 2024
spot_img

በሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠረችው ላምሮት ከማል በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት መቅረቧ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 30፣ 2013 ― ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በቀጥታ በፕላዝማ ችሎቱን የተከታተለችው ተከሳሿ ከዚህ ቀደም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ምርመራ ችሎት በቂ ማስረጃ አላገኘሁባትም ሲል በነጻ ካሰናበታት ወዲህ ፍርድ ቤት ስትቀርብ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡

በትላንትናው እለት የከሳሽ አቃቤ ሕግ እና የተከሳሽ ክርክር ለመስማት ያስቻለው ፍርድ ቤቱ፣ ተከሳሽዋ የአቃቤ ህግ የይግባኝ ወረቀት እንዳልደረሳት በመናገሯ ወደ ክርክሩ እንዳልተገባ ዶይቸ ቨለ ዘግቧል፡፡

በፕላዝማ ቀርባ ለፍርድ ቤቱ ሐሳቧን የገለጸችው ተጠርጣሪዋ ላምሮት ከማል፣ ለችሎቱ የቀረበችው በማረሚያ ቤት ትዕዛዝ መሆኑንና የይግባኝ ክሱን ጭብጥ ጉዳይ ለማግኘት ግን ማረሚያ ቤቱን ጠይቃ መከልከሏን ገልጻለች።

አቃቤ ሕግ በበኩሉ የይግባኝ ክስ ወረቀቱ ከመስሪያ ቤቱ ወጪ ሆኖ ወደ ማረሚያ ቤቱ መላኩን ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል። ተከላካይ ጠበቃ ይኑራት አይኑራት በፍርድ ቤቱ የተጠየቀችው ላምሮት ከማል፣ ከዚህ በፊት በከፍተኛ ፍርድ ቤት መንግሥት ያቆመላት ጠበቃ ቢኖርም ክሱ ግን እንዳልደረሰው ገልጻለች፡፡

ችሎቱም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላት እና የክስ ጭብጡን የሚገልጽ የአቃቤ ህግ ይግባኝ ለተከሳሽ በቤተሰቦቿ በኩል እንዲደርሳት እና ለሚቆምላት ጠበቃም ግልባጩ እንዲሰጥ ሲል አዟል። የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ ክሱ ላይ ለማከራከር ተለዋጭ ቀጠሮውን ለግንቦት 23፣ 2013 ሰጥቷል።

በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ የተጠረጠረችው ላምሮት ከማል ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 መሠረት በአቃቤ ህግ ተከሳ፤ የካቲት 18፣ 2013 ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽዋ ላይ ያገኘሁት የሰውና የሰነድ ማስረጃ በቂ ባለመሆኑ በነጻ አሰናብቷት እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img