አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሚያዝያ 29፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት የፊታችን እሑድ ግንቦት 1፣ 2013 በመስቀል አደባባይ ወይም በተለምዶአዊ አጠራሩ አብዮት አደባባይ ሊካሄድ የታቀደውን የጎዳና የኢፍጣር ዝግጅት በመቃወም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ደብዳቤ ጽፏል፡፡
የቤተ ክርስትያኒቱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በደብዳቤው ‹‹የመርሐ ግበሩ አላማ የሙስሊም ወገኖቻችንን ጾም ተከትሎ የኢፍጣር መርሐ ግብር እንዲካሄድ የተፈለገ ቢሆንም፣ በመስቀል አደባባይ በመሆኑ ተከባባሮና ተቻችሎ የኖረውን የሃይማኖት ተከታዮችን የሚያቃቅር ሆኖ የሁከት መነሻ እንዳይሆን›› በማለት አስፍሯል፡፡
አክሎም ‹‹የአፍጥር መርሐ ግብር ከዚህ ቀደም ለብዙ ዓመታት ሲካሄድ በነበረበት የአዲስ አበባ ስታዲየም መሆኑ እየታወቀ በምን ምክንያት በመስቀል አደባባይ እንዲካሄድ እንደተፈለገ ፍቃድ የሰጠው አካል ሊያጤነው ይገባል›› ብሏል፡፡
የቤተ ክርስትያኒቱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በማሳረጊያው ‹‹የአፍጣር መርሐ ግብሩ ለበርካታ ዓመታት በዓላቸውን ሲያከብሩበት›› ነበር ባለው ቦታ፣ ስታዲየም እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የተቃወመችው የፊታችን እሑድ ሊካሄድ የታቀደው የኢፍጣር ሥነ ሥርዐት ከአምስት ሺሕ በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ ግንባታ ላይ የሚገኘው መስቀል አደባባይ፣ በርካታ ሀገራዊና መልከ ብዙ ኹነቶችን ሲያስተናግድ የቆየ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከልም የሙዚቃ ትርኢቶችና ኮንሰርቶች ዋነኞቹ መሆናቸው ይታወቃል፡፡