አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሚያዝያ 29፣ 2013 ― የኬንያው ኢንሹራንስ ኩባንያ ጁብሊ ሆልዲንግስ እና የጀርመኑ አሊያንዝ ኩባንያ በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ገበያ ለመግባት ሐሳብ እንዳላቸው ዘ አፍሪካን ሪፖርት የተባለው ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
በኢንሹራንስ ገበያ በቀጠናው ከግዙፎቹ ተርታ ይመደባል የሚባልለት የጁብሊ ሆልዲንግ አለቃ ኒዛር ጁማ እንደገለጹት ከሆነ፣ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍ እንድታደርግ መጠየቁን አስታውሰው፣ የድርጅቱ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሊኖረው የሚችል መሆኑን በመጠቀስም ገበያው ክፍት ከተደረገ የኢንሹራንስ ገበያው ስለሚከተል ኢትዮጵያ በጣም ጥሩ የገበያ አማራጭ ትሆናለች ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ እርሳቸው የሚመሩት ጁብሊ ሆልዲንግም ከጀርመኑን አሊያንዝ ጋር እንደሚነጋገሩ አለቃው አክለዋል፡፡
የጀርመኑ አሊያንዝ በቅርቡ በጁብሊ ኩባንያ ከፍተኛውን የባለቤትነት ድርሻ የገዛ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ በጥምረት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት ከመንግሥት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል። ግዙፉ አሊያንዝ ኩባንያ 12 አፍሪካ አገራትን ጨምሮ፣ በዓለም በ70 ሀገራት የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት ዓይናቸውን የጣሉት ሁለቱ ኩባንያዎች በቅርቡ የመዋሃድ ሐሳብ እንዳላቸው ነው የተነገረው፡፡