Monday, October 7, 2024
spot_img

መንግሥት ‹‹ሸኔ›› የሚባል ድርጅት ሳይኖር በሽብርተኝነት መፈረጁ የኦሮሞ ድርጅቶችን ኢላማ ለማድረግ ያለመ ሊሆን እንደሚችል ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሚያዝያ 28፣ 2013 ― የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ተቀዳሚ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና መንግስት ‹‹ሸኔ›› እና ሕወሃትን በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ማድረጉ በፖለቲካው ላይ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም ብለዋል፡፡

ሸኔ የሚባል የፖለቲካ ፓርቲ አለመኖሩን በመጥቀስም መንግሥት ይህን ማድረጉ ‹‹በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን በተዘዋዋሪ መጥራት ይመስለኛል›› በማለት፣ ሥያሜውም ‹‹በኦሮሚያ አካባቢ በኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ኢላማ ያደረገ ስያሜ ይመስለኛል›› ብለውኛል ሲል ኢትዮ ኤፍ ኤም ዘግቧል፡፡

እንዲህ አይነት ፍረጃ የቀድሞ መንግሥትም ሲያደርገው የነበረ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ይህ ዓይነቱ ተግባር መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ቢሆን ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ አንደርስም ነበር፤ ይህም ተግባር ቀድሞ ከነበረው መንግስት የተለየ ነው ብዬ አላስብም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ተሰብስቦ ሕወሃት እና ‹ሸኔ›ን በሽብርተኝነት ከፈረጀ በኋላ በጉዳዩ ላይ ለሚዲያዎች የተናገሩት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዮስ በተለምዶ ‹ሸኔ› የሚባለው እራሱን ‹የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት› ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው ብለዋል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በሌሎችም ክልሎች እየተንቀሳቀሰ ጥቃት የሚያደርስ ነው ያሉት ድርጅቱ፣ ‹‹ሥያሜውን በተመለከተ እራሱ ለእራሱ የሰጠውን ሥያሜ ግን እኛ የምናፀድቅበት ምክንያት የለንም፤ ተገቢም አይሆንም ብለን እናምናለን ያሉ ሲሆን፣ ይህ ቡድን ከዚህ በፊት እንደ ‘ህወሓት’ ተመዝግቦ፣ ህጋዊ እውቅና፣ ህጋዊ ሰውነት እና ሰርተፊኬት ኖሮት የሚያውቅ አይደለም፤ ስለዚህ ስያሜው እሱ እራሱን በአንድ ስያሜ ይሰይማል፤ አንዳንዶች በሌላ ስም ይጠሩታል በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’ ይባል ነበር ስለዚህ በተለምዶ ከሚጠራበት ‘ኦነግ ሸኔ’/ ‘ሸኔ’ ከሚባለው ‘ሸኔ’ የሚለውን መርጠናል›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹እዚህ ጋር ግልፅ መሆን ያለበት በአዋጁ አንቀፅ 23 መሰረት ሥያሜውን ብትለዋውጥ ያው ቡድን ያው ስብስብ እስከሆነ ድረስ በውሳኔ ሀሳቡ የተገለፀው ስብስብ እስከሆነ ድረስ ስያሜ መለዋወጥ የሚያመጣው ለውጥ የለም፤ ውሳኔ ሀሳቡ ተፈፃሚ ይሆንበታል። አይ እኔ እራሴን የምጠራው እንዲህ ብዬ ነው፤ እንዲያ ብዬ ነው የሚለው ማምለጫ ሊሆን አይችልም›› ሲሉም ተናግረዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img